"የሚለማ እንጂ የሚዘጋ መንገድ የለንም" - የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
"የሚለማ እንጂ የሚዘጋ መንገድ የለንም" - የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

ኢዜአ ነሐሴ 12/2012 በኦሮሚያ ክልል የልማት፣ የሰላምና የስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ገለጹ።
የቢሮ ኃላፊው የክልሉን አጠቃላይ እንቅሰቃሴ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የበለጸገ አስተማማኝ ሰላም የተረጋገጠበት ሃገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የክልሉ መንግስት ከምንግዜውም በላይ በሁሉም እንቅስቃሴ የተናበበ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
የክልሉ ህዝብም አፍራሽ ኃይሎች ሩቅ ተቀምጠው በተደጋጋሚ የሚያደርጉትን ጥሪ በማክሸፍ ለክልሉ እንዲሁም ለሃገር ሰላምና ልማት ያለውን ቁርጠኛነት እያሳየ መሆኑን አውስተዋል።
"በዛሬው እለትም 'እኛ የሚለማ መንገድ እንጂ የሚዘጋ መንገድ የለንም፤ ለሰላምና ለልማት እንጂ ለአፍራሽ ወሬ ጆሮ የለንም' በሚል መርህ ለሚነዛው ወሬ በስራ ምላሽ ሰጥቷል" ብለዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ህዝቡ ለልማት፣ ለሰላምና ለጸጥታ እንዲሁም ለስርዓት ግንባታ ያለውን ታላቅ ቁርጠኝነት በክልሉ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች በወሩ ሲካሄዱ በነበሩ የሰላም ኮንፍረንሶች ላይ ሲገልጽ ቆይቷል።
"መንግስትም በየደረጃው የሚነሱትን የሰላምና የጸጥታ ችግሮች መቆጣጠርና የህግ የበላይነትን ያለ ምንም ማቅማማት መውሰድ እንዳለበት ህዝቡ አጥብቆ ጠይቋል" ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም በህጉና በህገ መንግስቱ የተሰጡትን ተልእኮዎች ለመወጣት በጠንካራ የህዝብ ድጋፍ የህግ የበላይነትን ለማስከበር አጠናክሮ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በየደረጃው ያሉትን መንግስታዊ መዋቅሮች በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በትጋት እየሰራ መሆኑን አውስተዋል።
"በለውጡ ተቃራኒ በቆሙ ሃይሎች አፍራሽ ጥሪ ሰበብ ዓይናችንን ከተያያዝነው የብልጽግና ግባችን፤ እንዲሁም እርምጃችንን ደግሞ ከተያያዝነው የአገርና የስርዓት ግንባታ መንቀል የለብንም ሲሉ" ገልጸዋል።