የኤርትራ መንግስት ማዕቀቦች እንዲነሱለት የሚያስችል ተጨባጭ ለውጥ አላመጣም-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

67
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 የኤርትራ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የጣለበት ማዕቀችቦ እንዲነሱለት የሚያስችል ተጨባጭ እርምጃ  እየወሰደ አለመሆኑን ኢትዮጵያ ገለጸች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የሶማሊያና የኤርትራ ማዕቀብ ኮሚቴ አባላትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው አገራት አምባሳደር ተወካዮችን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ በጣላቸው ማዕቀቦች ተፈጻሚነት ዙሪያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድና በባህረ ሰላጤው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። የኤርትራ መንግስት የጸጥታው ምክር ቤት የጣላቸው ማዕቀቦች እንዲነሱ የሚያስችል ተጫባጭ እርምጃ እየወደሰ እንዳልሆነ  በውይይቱ ወቅት መገለጹንም ነው አቶ መለስ ያብራሩት። "እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ የተጣለው ማዕቀብ በኛ በኩል እንዲነሳ የሚያስችል ተጫባጭ ሁኔታ መሬት ላይ የለም የሚል እምነት አለን” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “የኤርትራ መንግስት ቀደም ሲል ካለው ባህሪው ለውጥ ባላመጣበት ሁኔታ ማዕቀቡን የማለሳለስ ጉዳይ አካባቢው ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል" ብለዋል። ኢትዮጵያ ከሶማሊያና ኤርትራ ማዕቀብ ኮሚቴ ጋር በትብብር እንደምትሰራና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ሚኒስትር ዴኤታዋ ለኮሚቴው አባላት መግለጻቸውንም ተናግረዋል ቃል አቀባዩ። የኮሚቴው የወቅቱ ሊቀመንበር ካዛኪስታናዊው አምባሳደር ኬራት ኡማሮቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለኮሚቴው እያደረገች ላለው ድጋፍ ማመስገናቸውንና በቀጣይ ዳጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥልም መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ኮሚቴው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በጅቡቲ፣ ኬንያና ሶማልያ ጉብኝት ማድረጉንና በጉዳዩ ዙሪያ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መቀመጫ ኒው ዮርክ እንደሚመክርበትም ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በባህረ ሰላጤው ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የያዘችውን አቋም አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለጿንም ነው አቶ መለስ ያስረዱት። "በባህረ ሰላጤው የተከሰተው ችግር በአፍሪካ ቀንድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚፈጥር የኢትዮጵያ መንግስት የአካባቢው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የጸና አቋም እንዳለውና በኩዌቱ ኤሚር አልሳባህ የተጀመረውን ጥረት እንደምትደግፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸውላቸዋል" ብለዋል። የሶማሊያ መንግስት ሰላምን ለማስፈን እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአገሪቷ የጸጥታና ኢኮኖሚ መዋቅሮች እንዲጠናከሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ኢትዮጵያ ገልጻለች ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለመፍታት በምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ለጀመረው ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም አቶ መለስ አክለዋል። የሶማሊያና የኤርትራ ማዕቀብ ኮሚቴ የተቋቋመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ  በ1992 በሶማሊያ እንዲሁም  እ.ኤ.አ በ2009 በኤርትራ ላይ የጣላቸውን የጦር መሳሪያ፣ የጉዞና የንብረት ማንቀሳቀስ ማዕቀቦችን ተፈጻሚነት ለመቆጣጠር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም