በኢትዮጵያ አዲሱ የጀርመን አምባሳደር የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጅ አቀረቡ

78

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 12/2012 ( ኢዜአ)  በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኡር የሹመት ደብዳቤ ቅጅ አቀረቡ።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር በመሆን የተሾሙትን አምባሳደር ስቲፈን ኡር የሹመት ደብዳቤ ቅጅ በዛሬው እለት ተቀብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ላላት ግንኙነትና ትብብር ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ ገልጸው፤ ጀርመንም ለኢትዮጵያ ስለምታደርገው አጠቃላይ ድጋፍ አምባሳደር ሬድዋን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በነበራቸው ውይይት የሁለቱ አገሮች ትብብር አሁንም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተም አምባሳደር ሬድዋን ገለጻ አድርገውላቸዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኡር በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አጠቃላይ ለውጥ በተመለከተ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ላይ ትኩረት ማድረጓ የአገሪቱን አጠቃላይ እድገት ለማፋጠን እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

ጀርመን በዘርፉ ያላትን የካበተ ልምድ ለማካፈል ትሰራለችም ብለዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሶስቱ አገሮች ያላቸውን ልዩነት የሁሉንም አገራት ጥቅም ባማከለ መልኩ በውይይት መፍታት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም