የኮቪድ 19 በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር በአፍሪካውያን የተሰሩ 10 የፈጠራ ውጤቶች

557

ነሀሴ 10/2012 (ኢዜአ) በአፍሪካ የፈጠራ ባለሙያዎች የኮቪድ 19 በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ የፈጠራ ውጤቶች ተሰርተዋል።

ከተሰሩት ምርቶች መካከል አስር የፈጠራ ውጤቶችን  ቢቢሲ በዘገባው ተመልክቷቸዋል።

‘ዶክተር ካር’ የተሰኘው ሮቦት በሴኔጋል ዳካር የፖሊ ቴክኒክ ተማሪዎች የተሰራ ሲሆን የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ  ከተያዙ ታካሚዎች ጋር የሚፈጠረውን ንክኪ ለመቀነስ የሚያስችል ነው።

ሮቦቱ ካሜራ የተገጠመለትና በርቀት በመተግበሪያ አማካኝነት ለመቆጣጠር የሚቻል ነው።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ እንደገለጹት፤ ሮቦቱ በታካሚ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ሙቀት መለካት፣ መድሃኒቶችና መድሃኒቶችን ማቅረብ ይችላል።

የቱኒዚያ መሃንዲሶች በኦን  ላይን  ሳንባን በጨረር በመርመር አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙንና አለመያዙን ለመለየት የሚያስችል ፈጠራ ሰርተዋል።

የአገሪቱ ተመራማሪዎች መሳሪያው ቫይረሱን የመለየት እድሉ 90 በመቶ መሆኑን መግለጻቸውና ስራው በሂደት ላይ እንደሆነም በዘገባው ተመልክቷል።

በቱኒዚያ  ዋና ከተማ ተግባራዊ የተደረገውን ከእንቅስቃሴ ዝግ የማድረግ እርምጃ ለመቆጣጠር የሚያስችል የፖሊስ ሮቦት ሌላው በአገሪቱ የተሰራ የፈጠራ ውጤት ነው።

በደቡብ አፍሪካ የኮቪድ 19  ምርመራ ውጤት እስከ ሶስት ቀናት ሊፈጅ የሚችል ሲሆን፤ በ65 ደቂቃዎች ውስጥ ውጤት የሚሰጥ ማሽን በደቡብ አፍሪካውያን የፈጠራ ባለሙያዎች ተሰርቷል።

የመርመሪያ ማሽኑ ከመጸደቁና ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት የቁጥጥር ሂደቶችን ማለፍ እንደሚገባውም ተመልክቷል።

በደቡብ አፍሪካዊቷ ወጣት  በአንድ ቀን 100 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማምረት የሚችል  ‘ስሪ ዳይሜንሽናል ማተሚያ’   በጆሀንስ በርግ ሆስፒታሎች ጥቅም ላይ መዋሉም ተገልጿል።

በኬንያ የብር ኖቶችን በኬሚካል የሚያጸዳ ከእንጨት የተሰራ ሳኒታይዘር መሳሪያ የተሰራ ሲሆን፤ የብር ኖቶችን ማሽኑ ውስጥ በማስገባት ለማጽዳት የሚያስችል ነው።

በአንድ የዘጠኝ አመት ኬንያዊ ተማሪ የተሰራ ንኪኪን የሚያስቀር በእግር በመርገጥ የሚሰራ አውቶማቲክ የእጅ መታጠቢያም በአፍሪካ ከተሰሩ የፈጠራ ውጤቶች መካከል ተጠቅሷል።

በጸሀይ ብርሃን የሚሰራና ሰዎች እጃቸውን ወደ ማሽኑ ሲያስጠጉ ውሃና ሳሙና የሚረጭ የእጅ መታጠቢያ የተሰራው ደግሞ በጋናዊው ሊስትሮና ወንድሙ ሲሆን፤ ማሽኑ  ከ25 ሰከንዶች በኋላ ውሃና ሳሙና ማፍሰሱን ያቆማል።

በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የመተንፈስ ችግር ላጋጠማቸው ታካሚዎች ጥቅም ላይ የሚውል አውቶማቲክ የመተንፈሻ አጋዥ መሳሪያ በአንድ ናይጄሪያዊ ተማሪ መሰራቱም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ የጸጉር አስተካካዮች የቫይረሱን ንኪኪ ለመቀነስ በተከለለ ክፍል ሆነው የደንበኞቻቸውን ጸጉር ማስተካከል የሚቻልበት ፈጠራ መስራታቸውም በዘገባው ተካቷል።