በአፋር ክልል ለጎርፍ አደጋ ተጎጂዎች የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገ ነው-- የክልሉ መንግስት

79

ሰመራ ፣ ነሀሴ 10/2012 ( ኢዜአ) በአፋር ክልል በጎርፍ ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የክልሉ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን እንደገለጹት፤ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ የተከሰተው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ በርካቶችን አፈናቅሏል።

በአደጋው እስከ አሁን የሰው ህይወት ባያልፍም ከፍተኛ ቁጥር ባለው አርብቶ አደር ህብረተሰብና በእንስሳቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍ ያለ እንደሆነ አብራርተዋል።

አቶ መሀመድ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ችግሩ ይበልጥ ጉዳት እንዳያደርስ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የክልልና የፌዴራል መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠትም የተለያዩ አማራጮች  ተግባራዊ  እንደ ሚደረግ  ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ስራዎች  እየተከናወኑ  ነው  ብለዋል።

ከረጅም ጊዜ አኳያም ስራዎችን በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር አስፈላጊ የመፍትሄ እርምጃዎች እንደሚወስዱ ሀላፊው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም