በግንዛቤ ላይ በተመሰረተ ስራ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት መግታት ያስፈልጋል --የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር

59

ሐዋሳ፣ነሀሴ 10/2012 (ኢዜአ) አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት የተጠናከረ ህዝብን የማነቃነቅ፣ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ወሳኝ መሆኑን የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ላለፉት አራት ወራት በኮሮና መከላከል ስራ በከተማዋ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ላበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ በማመስገንና በቀጣይ ርምጃዎች ላይ ትላንት ምክክር አድርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ካንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የግብዓት አቅርቦት ውስንነንት በሚታይበት ወቅት ትልቅ መስዋእትነት ከፍለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎች ምስጋና ይገባቸዋል።

“በከተማዋ በጤናው ዘርፍ በግል የተሰማሩ ባለሃብቶችና ባለሙያዎች የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው የህክምና ማዕከላቸውን፣ ግብአት፣ ባለሙያዎችንና ገንዘባቸውን ጭምር በመስጠት ላሳዩት ቀናነት ክብር ይገባቸዋል” ብለዋል።

የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገሩት አቶ ጥራቱ ችግሩን ለመፍታት ማህበረሰቡን በማነቃነቅ፤ በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ አሁንም ከጤና ባለሙያዎች ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በትራንስፖርት አገልግሎት፤ በገበያ፤ በኢንዱስትሪ ፓርክ፤ ነዳጅ ማደያዎች፤ ሆቴሎች፤ ምግብ ቤቶችና የጀበና ቡና መሸጫዎች የሚስተዋለው ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ ለቫይረሱ ስርጭት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡

“የሃይማኖት ተቋማት መደበኛ የአምልኮ ፕሮግራም መጀመራቸው፤ ሰርግ፤ ለቅሶና ሌሎች ማህበራዊ ሁነቶች ከዚህ በፊት እንደተለመደው መቀጠላቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ያመላክታል” ብለዋል።

ይህን ለመፍታትም ከቤተ ዕምነት መሪዎች፤ የሃገር ሽማግሌዎችና ዕድር መሪዎች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ቫይረሱ በከተማው ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ በጎ ፈቃደኞች፤ ባለሙያዎችና ተቆርቋሪ የሆነ ሁሉ ማህበረሰቡን ለመታደግ የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የከተማው ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙንጠሻ አብርሀም ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ባለሙያዎች እየተያዙ በመሆናቸው የሚፈጥረው መደናገጥ የስርጭት መጠኑን በመከላከልና ሌሎች በሽታዎች ህክምና አሰጣጥ ላይ ስጋት እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ጉዳዩ የእኛ ነው" ያሉት የጤና መምሪያው ሃላፊ “ባለሙያዎች ከዚህ በመውጣት በገቡት ቃል መሰረት የተጀመረውን ጦርነት ለማሸነፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆን ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ የኮሮና ህክምና ኦፕሬሽን አስተባባሪ ዶክተር ሃኒባል አበራ በበኩላቸው በከተማዋ ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ 3 ሺህ 984 ናሙናዎች ተወስደው 312 ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጸዋል።

በሽታው በአብዛኛው ምልክት ሳያሳይ የሚቆይ መሆኑ ባህሪውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገልጸው ማህበረሰቡ ማስክ በመጠቀም፤ ንጽህናውን በመጠበቅና በመራራቅ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችና የጸጥታ አካላት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ዘላለም መርሹ እንዳሉት ቤት ለቤት በመሄድ በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

በሃዋሳ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት መደበኛ አምልኮ መጀመሩ ስጋቱን ከፍተኛ እንዳደረገው በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የሃዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ወሰንየለህ ስምኦን ተናግረዋል፡፡

መዘናጋትን ለማስቀረት የወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላዎችም ተግባራዊ እንዲደረጉም ጠይቀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም