ፕሮጀክቶቹ ከተማዋን ከመመጠን ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ የሚያደርጋት ነው

431

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ውስጥ የሚከናወኑ የማስዋብ ፕሮጀክቶች ከተማዋን ከመመጠን ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ የሚያደርጋት መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ፕሮጀክቶቹ በአጭር ግዜ መጠናቀቃቸው ትልቅ ስኬትና ሌሎች ፕሮጀክቶች በአርዓያነት ሊወሰዱ እንደሚገባም ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ወጣት ይትባረክ ተሾመ ከስምንት ዓመት በፊት የአራት ኪሎ ነዋሪ እንደነበር አስታውሶ፤ አካባቢው በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲህ ሆኖ ማየቱ የሚያስደስት መሆኑን ገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ ለነዋሪውም ለከተማውም የሚመጥን መሆኑን አንስቷል።    

እንደ ወጣት ይትባረክ ገለጻ በአዲስ አባባ የሚገነቡ ሌሎች ፕሮጀክቶች ከዚህ ልምድ መውሰድ ይገባቸዋል ብሏል።  

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሰለሞን አሸብር በበኩላቸው በአዲስ አበባ የተከናወኑ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ ”በአዲስ አበባ እንዲህ ይሰራል ወይ ብዬ ራሴን ለመጠየቅ ተገድጃለሁ” ይላሉ። 

ሥራው አዲስ አበባን ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።   

በተለይም ቤተ መንግሥቱ በፊት የሚፈራ ግቢ እንደነበር በማስታወስ አሁን ክፍት መደረጉ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ጽዱና ውብ ሆኖ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጎብኝዎች ክፍት መደረጉን አድንቀዋል።

”ፕሮጀክቶቹ የሚፈለገውን ጥቅም እንዲሰጡ ነዋሪው በየኔነት ስሜት መንከባከብ አለበት” ሲሉ ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ ”መናፈሻዎች አካባቢ ጫትና ሲጋራ የመሳሰሉ ሕገወጥ ድርጊቶች መቆም አለባቸው” ብለዋል።

በተለይም የሕግ አካላት ቁጥጥር ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።   

ወይዘሮ ሺብሬ ኪዳኔ እንደሚሉት ደግሞ፤ በመንግሥት በኩል የተጀመሩ መሰል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፤ ሕዝቡም በሚችለው መጠን ጎብኝቶ ስለ አገሩ ማወቅ አለበት።   

ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክ የሚያሻግር ሥራ መሰራቱን መታዘባቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሺብሬ፤ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ተናግረዋል።