በመጪው መስከረም ወር እምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል የዘመቻ ሥራ ይከናወናል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

99

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9/2020 (ኢዜአ) በመጪው መስከረም ወር እምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚያስችል የዘመቻ ሥራ እንደሚከናወን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት ተደርጓበታል።

ስትራቴጂክ ዕቅዱ አረሙን ማስወገድ፣ በዘላቂነት የውኃና አካባቢ ጥበቃ መሥራትና ነፃ የሀይቅ ዳርቻ መሥራት እንዲሁም በሀይቁ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ዕቅዱ ላይ ገለጻ ያደረጉት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የእምቦጭ አረም በ1956 ዓ.ም በአባ ሣሙዔል ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ መጤ ወራሪ አረም መሆኑን ይገልጻሉ።

ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሀይቅ ላይ አረሙ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን በአማራ ክልል በሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና 35 ቀበሌዎች መዳረሱን ተናግረዋል።

እምቦጭ አረም በብዝሃ ሕይወት አንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በጣና ሀይቅና በአጠቃላይ በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የውኃ አካላት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ከከተማና ከኢንዱስትሪ ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ፍሳሾች አረሙ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ይሁንና አረሙን ማስወገድ የሚቻለው ልማዳዊ ከሆነ አሰራር ወጥቶ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮች በማየት እምቦጭ አረምን ለኃይል አማራጭነት መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።

የእምቦጭ አረምን ለመከላከል በጣና ተፋፈስ ዙሪያ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በተለይም የተለያዩ ፈሳሾችና ንጥረ ነገሮች ወደ ሀይቁ እንዳይገቡ የማድረግ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮም ከ21 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በተፋሰሱ ዙሪያ በመተከሉ እምቦጭ አረሙን በነባር አገር በቀል ዝርያዎች የመተካት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በጣና ተፋፈስ ዙሪያ በአንድ ሺህ ሄክታር ላይ ለሚሰራው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ሚኒስቴሩ 36 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል።

በተመደበው በጀትም ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ገባር ወንዞችን ከፈሳሾችና ከንጥረ ነገሮች የመጠበቅ እንዲሁም ብዝሃ ሕይወቱን የመንከባከብ ሥራ እንደሚከናወን ነው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ያስረዱት።

ለስትራቴጂክ ዕቅዱ ማስፈጸሚያ 300 ሚሊዮን ብር በሚኒስቴሩ መመደቡንና 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ከአጋር ድርጅቶች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

''በአጠቃላይ አረሙን ለመከላከል ሁሉን አቀፍ የሆነ የመፍትሔ አማራጭ መከተል ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በወቅቱ እንደገለጹት፤ የእምቦጭ አረም በጣና ሀይቅና በሌሎች ሥነ ምህዳሮች ላይ የደቀነውን ሥጋት ጊዜ የማይሰጠውና ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ ነው።

በአካባቢው ያለው ማኅበረሰብም ከሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ ሥራዎችን ቶሎ ወደ ሥራ በማስገባት የተቀረውን ሥራ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ መምራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በዚሁ መሠረት በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም እምቦጭ አረምን የማስወገድ ዘመቻ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ለዘመቻው የሚያስፈልገውን የቴክኖሎጂ አማራጭ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

እምቦጭ አረም ቶሎ መፍትሔ ካላገኘ አሁን እየተገነባ ላለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ሥነ ምህዳሮች ሥጋት ስለሆነ ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መንግሥት ለማሽኖች ለሚያስፈልጉ ግዢዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ አሁን ያሉ የቴክኖሎጂ አማራጮች መጠቀምና ማሽኖችን በመከራየት የአጭር ጊዜ ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

ለስትራቴጂክ ዕቅዱ ውጤታማነት ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ሥራቸውን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም