በሻሸመኔ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አንድ ሚሊዮን 600 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

39

ሀዋሳ፣ ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) በቅርቡ በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አንድ ሚሊዮን 600 ሺህ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

በስፍራው ዛሬ የተደረገው ይሄው ድጋፍ  በሴቶች ፣ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር እና በፌዴራል ብልፅግና ፓርት ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት የተገኘ ነው።

በዚህ ወቅት  የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወጣት አስፋው ተክሌ እንዳለው በድጋፉ የአዲስ አበባ፣የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ወጣቶች የምግብ ዱቄት፣ግንባታ ቁሳቁስ፣አልባሳትና የመኝታ ፍራሽ በመስጠት ተሳትፈዋል።

በከተማዋ በደረሰው ጥፋት  የተጎዱትን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኘውን ወጣት በማስተባበር ከህዝባችን ጎን እንቆማለን ብሏል።

የቁሳቁስ ድጋፉን ለሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ያስረከቡት የሴቶች ፣ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ በበኩላቸው የሃገሪቱን ለውጥ ለመቀልበስ በሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሰለባ በመሆናችሁ እጅግ አዝነናል ብለዋል።

ሆኖም  ሻሸመኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀድሞ የንግድ ቀጠናነቷ እንደምትመለስ እምነታቸው መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ የዓለም ወጣቶችን ቀን በዓልን በማስመልከት ከወጣቶች ጋር  አጋርነታቸውን ለማሳየትና ከጎናችሁ መሆናችንን ለማረጋገጥ በማሰብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ከፍታ በሴረኞች  ጥፋት  የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የጀመርነውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በአንድነት በመሆን የፀረ ሰላም ኃይሎችን እኩይ እንቅስቃሴ ለማምከን የተጀመረው የወጣቶች ድጋፉ እስከታችኛው መዋቅር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  የገለጹት ደግሞ በፌዴራል ብልፅግና ፓርቲ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ሁሳ ናቸው።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጉታ ቾሬ በበኩላቸው የከተማው ወጣቶች  የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት ተከትሎ ሀዘናቸው ለመግለጽ የወጡ ሰዎችን ሽፋን በማድረግ ጥቂት የተደራጁ የጥፋት ኃይሎች ሁኔታውን በሌላ  አቅጣጫ በማዞር ከፍተኛ ውድመት ማድረሳቸውን  አስታውሰዋል።

አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ፣ከተማዋንም ወደ ቀድሞ ሰላሟ ለመመለስና ተጎጂዎችን ለማቋቋም አስተዳደሩ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በዕለቱ ድጋፍ ከተደረገላቸው የሻሸመኔ ተጎጂዎች መካከል መምህር ደብሪቱ ሃይሌ በሰጡት አስተያየት  6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሞባቸው ሀዋሳ ዘመድ ጋር እንደተጠለሉ ገልጸው፤ “ሀብት ተሰርቶ ይገኛል ሰላም ነው የምመኘው “ብለዋል።

ሌላዋ ተጎጂ ወይዘሮ ሰርካለም የሸዋስ  በበኩላቸው የፈረሰባቸውን ቤት መልሶ ለመገንባት የከተማው አስተዳደርና ወገን ከጎናቸው መቆሙን በመግለጽ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።