ማዕከሉ አረጋውያንን ከጎዳና ለማንሳት ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጠው ጠየቀ

39

አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2012(ኢዜአ) መቄዶኒያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከሁለት ሺህ በላይ በጎዳና የወደቁ አረጋዊያንን አዕምሮ ህሙማን ለማንሳት ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲሰጠው ጥሪ አቀረበ።
ማዕከሉን ለመርዳት ቃል የገቡ ወገኖችም ቃላቸውን እንዲፈጽሙ ጠይቋል።

ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ወር ውስጥ በጀመረው አረጋዊያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና እያነሳ መሆኑን ገልጿል።

የማዕከሉ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ራጁ ዲንሳ ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ በአዲስ አበባና ሐረር ከተሞች ከሁለት ሺህ በላይ አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማንን ከጎዳና ለማንሳት እየሰራ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ ከሁለት ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአእምሮ ህሙማንን ለማንሳት ማቀዱንና እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ ከጎዳና መነሳታቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሐረር ከተማ ለማንሳት ከታቀደው 110 አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማን መካከል 60ዎቹን ማንሳቱን አስታውቀዋል።

በመሆኑም በከተሞቹ  ዕድሚያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋዊያንንና ጎዳና ላይ የወደቁ ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን ጥቆማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።ጥቆማ ለመስጠት በ90-49-49-49-49 ወይንም በ90-70-70-70-70 ስልክ ቁጥሮች ደውሎ ማሳወቅ እንደሚቻል አቶ ራጁ አስረድተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ማዕከሉን መጎብኘት ባለመቻሉ የሚደረገለት ድጋፍ ተቀዛቅዟል።

በወረርሽኙ ምክንያት መጋቢት 6 ቀን 2012 በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ቃል የገቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቃላቸውን እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል።

በወቅቱ ቃል ከተገባው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን እስካሁን የተሰበሰበው ከ15 ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ ነው የተናገሩት።

በመሆኑም በተሰጡት የስልክ ቁጥሮች በመደወል ቃል የገቡበትን ገልጸው ሕጋዊ በሆነ ደረሰኝ ያሉበት ድረስ በመሄድ መቀበል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በማዕከሉ የአረጋዊያን ተጠሪ መምህር ሳሙኤል ከበደ በማዕከሉ የሚገኙ አረጋዊያን የሚጦሩት ድጋፍ በሚያደርጉ ወገኖች በመሆኑ ቃል የገቡ አካላት ቃላቸውን አክብረው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት አረጋዊያንን መጎብኘት ባይቻልም፤ የማዕከሉ መግቢያ በር ላይ በሚገኘው ገንዘብ ቤት ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።

አልባሳትና ሌሎች ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖች በማዕከሉ ተገኝተው መለገስ ካልቻሉ፥ ያሉበት ድረስ በመሄድ መቀበል እንደሚቻልም ተጠቁሟል።

መቄዶኒያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከሶስት ሺህ ለሚበልጡ አረጋዊያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና በማንሳት የምግብ፣ የሕክምና፣ መጠለያና ሌሎች አገልግሎት ይሰጣል።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖች ቁጥር 10 ሺህ ለማድረስ እየሰራ ነው።

ማዕከሉ በአዲስ አበባ አያት አካባቢ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ ሆስፒታልና ለአረጋዊያን መኖሪያ የሚውል ባለ 11 ወለል ህንጻ እያስገነባ መሆኑም ታውቋል።