ሚኒስቴሩ በቀጣይ በአሰሪና ሰራተኞች የስራ ላይ ደህንነት ዙሪያ በትኩረት እንደሚሠራ አስታወቀ

69

አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2012(ኢዜአ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር በቀጣዮቹ 10 አመታት በአሰሪና ሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት በትኩረት እንደሚሠራ አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በ10 አመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋየ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በቀጣዮቹ 10 አመታት ለአሠሪና ሠራተኞች የሙያ ላይ ደህንነት፣ የሠራተኞች የመደራጀት መብት፣ የሥራ ላይ አደጋዎችን ለመቀነስ ትኩረት ይደረጋል።

በውጭ አገር የሥራ ስምሪት ላይም የዜጎችን ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ የሥራ እድል የመፍጠር ሥራ በስፋት ይከናወናል ብለዋል።

ወደ ውጭ አገራት ለሠራ የሚሄዱ ዜጎች የተቀናጀ አገልግሎት ባለመኖሩ እና ሰፊ ውጣ ውረድ በመኖሩ ዜጎች የሚደርሰውን እንግልት ፋራቻ በህገወጥ መንገድ የሚሄዱ እናዳሉ ጠቁመው፤ አሠራሩን በተቀናጀ መልክ በመሥራት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንም መታቀዱንም ተናግረዋል።

የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልም ቀጣይነት ባለው መንገድ ማደራጀት የሚያስችል የተጠና አሠራር ለመዘርጋት መታቀዱን ገልጸዋል።

አረጋውያን ያላቸውን የህይወት ተሞክሮ ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስተላልፉ የሚችሉበትና እነሱም ገቢ ሊያገኙ የሚችሉባቸውን ማዕከላት በመገንባት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷልም ነው ያሉት።

በሥራ አድል ፈጠራም ዜጎች በውጭ አገርም ይሁን በአገር ውስጥ በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሳተፉ የማድርግ ሥራ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

በእቅዱ ላይ በነበረው ውይይት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በአማካይ የ10 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እቅድ መያዙ ይታወቃል።

በእቅዱ መሰረት በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የማድርግ አላማ ተይዟል።

አገራዊ የልማት እቅዱ በግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን ሀብት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ የሰው ሃብት፣ የከተማ እና የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም