በአዲስ አበባ "የሞባይል መታወቂያ አገልግሎት" ሥራ ላይ ሊውል ነው

102

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 8/2012 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች መረጃቸውን በቀላሉ የሚያገኙበት ''የሞባይል መታወቂያ አገልግሎት'' ሊተገበር መሆኑን የከተማዋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው ለሶስተኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሳምንት በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በግብጽ፣ ግሪክና በጣልያን (ሮም) በእምነት ተቋማት አማካኝነት እንደተጀመረ ይታወቃል።

በመንግሥት ደረጃ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የተጀመረው ደግሞ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያም መንግሥት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የጀመረው በአዲስ አበባ በ1930ዎቹ እንደሆነ የከተማዋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ያመለክታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ እንዳሉት የከተማዋን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መረጃ ወደ ዲጂታል የሚቀይር አሰራር ሥራ ላይ ውሏል።

በቀጣይም የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ "የሞባይል መታወቂያ አገልግሎት" ሥራ ላይ ለማዋል መሳሪያዎች እየተገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"የሞባይል መታወቂያ አገልግሎት" ዜጎች በቀበሌያቸው የሚሰጡት አሻራ በኤጀንሲው የመረጃ ማዕከል ይቀመጣል ብለዋል።

መረጃው ማንኛውም ተቋም የተገልጋዮች መረጃ ትክክል መሆን አለመሆኑን በቀላሉ በሞባይል ስልክ ማረጋገጥ እንደሚችልበት ዶክተር ታከለ ገልጸዋል።

የፋይናንስና የመድን ተቋማት፣ ትራፊክ ፖሊስና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የግለሰቦችን መረጃ ለማጣራት እንደሚቻል አስረድተዋል።

መሳሪያውን ወደ አገር ቤት ለማስገባት በከተማ አስተዳደሩ በጀት ተይዞለት በግዥ ሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረበት 1935 ጀምሮ ያሉት የወረቀት መረጃዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጅታል ለመቀየር ሂደት ላይ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለፍትህ ስርዓት መስፈን የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ለዜጎች ህጋዊና አስተዳደራዊ አገልግሎት ለመስጠት፣ ሰብዓዊ መብትን ለማክበር ለፍትህና ማኅበራዊ አገልግሎት መረጃ ወደ ዲጂታል እንደሚቀየር ተናግረዋል።

በዚህም 104 ሺህ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ እንዲሁም ለ600 ሺህ ዜጎች የልደት፣ የጋብቻና የሞት የምስክር ወረቀት በዲጂታል አገልግሎት መስጠት እንደተቻለም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም