ኢትዮጵያ ብቁና ተወዳዳሪ ባህርተኞችን በማፍራት የውጭ ምንዛሪዋን ለማሳደግ እየሰራች ነው-ባለሥልጣኑ

87

አዲስ አበባ ነሐሴ 8/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ባህርተኞችን በማፍራት የውጭ ምንዛሪዋን ለማሳደግ እየሠራች መሆኗን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን አስታወቀ።

አገሪቱ በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ''ከፍተኛ ጥቅም'' የምታገኝበት ዕድል እንዳላት ይጠቀሳል።

በዘርፉ ያለውን አቅም በማሳደግ  ገቢውን የሚጨምሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ይገልጸል።

ከእነዚህም በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊና ተወዳዳሪ  ባህርተኞችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን አውስቷል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ ባህርተኞችን ማፍራት በሥራ ዕድል ፈጠራም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ረገድ  ጥቅም አለው።

ኢትዮጵያ ባህርተኞቿን በማሰልጠንና በዓለም አቀፍ የመርከብ ኩባንያዎች በማስቀጠር ለባለሙያዎቹ ሥራ በመፍጠር ለአገሪቱም ጥቅም ለማስገኘት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን 4 ሺህ የሚሆኑ ባህርተኞች በምስራቅ አፍሪካና በሌሎች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መቀጠራቸውን  ገልጸዋል።

ከዚህም በዓመት 24 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም  ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። 

ባለሥልጣኑ ሥራውን የሚያስፋፋበትና የሚያሳድግበት ”ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ” እያዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ስትራቴጂው በሚቀጥሉት10 ዓመታት ውስጥ እስከ 100 ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎችን ለማፍራትና እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ በውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ማቀዱን  አቶ መኮንን ገልጸዋል። 

በዓለም ባህርተኞችን በማፍራት ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል ፊሊፒንስ በዓመት ከ300 እስከ 400 ሺህ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰማራትም እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንደ ቻይና፣ ሕንድና ሩሲያ የመሳሰሉት አገሮችም ባህርተኞችን በማፍራት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም