የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ''ማስክ ኢትዮጵያ'' ዘመቻ ይፋ ሆነ

90

አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ የንቅናቄ ዘመቻ አካል የሆነው ''ማስክ ኢትዮጵያ'' በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የዘመቻውን መጀመር አስመል ክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ዘመቻው ለአጠቃቀም ቀላል የሆነውን ማስክ በአግባቡ በመጠቀም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያለመ መሆኑን አብራር ተዋል።

በዓለማቀፍ ደረጃ ቀላልና የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ የተረጋገጠለት ማስክ መጠቀም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

ማስክን ማድረግ ባህል እንዲሆንና ወረርሽኙ እስኪያቆም ድረስ ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም ''ማስክ ኢትዮጵያ" ከዛሬ ጀምሮ መተግበር ይጀምራል ብለዋል።

ዘመቻውን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደሚያስጀምሩትም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

በአገሪቱ ማስክ የማድረግ ባህል በሁሉም ክልሎች በእኩል ደረጃ እየተተገበረ ባለመሆኑ በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ተሞክሮ እንዲሰፋ ዘመቻው ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀላሉ የሚገኘውን ከህክምና ማስክ  በጨርቅ የተሰራ ማሳክ መጠቀም የበለጠ ተመራጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማስከ መጠቀም ብቻውን ቫይረሱን ይከላከላል ማለት ሳይሆን ሌሎች የ''መ' ህጎችን በመተግበር በቫይረሱ ከመያዝና ለሌላው ከማስተላለፍ መከላከል ያስችላል ብለዋል።

ማስክ ኢትዮጵያ በተለየ መልኩ ተግባራዊ ለሚያደርግና በፎቶ ግራፍ፣ በቪዲዮና በሬዲዮ የ30 ሰከንድ

ድምጽና ምስል ቀርጸው ለሚልኩ ሰዎች ውድድር ተዘጋጅቷል።

ለዚህ ውድድርም ሽልማት መዘጋጀቱን ዶክተር ሊያ ይፋ አድርገዋል።

ለሽልማቱ እስክ ነሃሴ 18 በሚካሄደው ውድድር በተቋሙ ዌብሳይት ላይ በሚለቀቀው አድራሻ መላክ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።  

በአገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱና ለዚህ የሚሆን ምላሽ የህብረተሰቡ የመከላከል ሁኔታ ባለማደጉ የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ መጀመሩን አስታውሰዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄው በክልሎች መጀመሩን የተናገሩት ሚንስትሯ ሁሉም ለተግባራዊነቱ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት የመመርመር አቅም በቀን 14 ሺህ መድረሱን አመልክተው በቀጣይ ሁለት ሳምንት 200 ሺህ  ሰዎች ለመመርመር እቅድ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም