ሎጎ ሀይቅን ከደለል እና ከብክለት ለመታደግ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው

64

ደሴ ነሐሴ 8/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ተውለደሬ ወረዳ የሎጎ ሀይቅን ከደለል ሙላትና ብክለት ለመታደግ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይድ ይብሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሀይቁ  በተራሮች መራቆትና  በእርሻ መስፋፋት በደለል የመሞላትና የብክለት አደጋ ተጋርጦበታል ።

ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ በዙሪያው የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።

ከተራሮችና እርሻ ማሳዎች  በጎርፍ እየታጠበ ወደ ሀይቁ የሚገባን ደለል  ለማስቀረት በበጋው ወቅት እርከንና ክትር ጨምሮ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል ።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተከናወኑባቸው ስፍራዎች በተያዘው ክረምት ከ120 ሺህ በላይ የዛፍ ችግኝ መተከሉንም አመልክተዋል ።

አቶ ሰይድ እንዳሉት በሀይቁ ዙሪያ የሚገኙ 700 የሚሆኑ አርሶ አደሮች የሰብል ማሳቸውን በቋሚ የፍራፍሬ ሰብሎች በመቀየር እንዲያለሙ እየተደረገ ነው።

እስካሁንም  በ30 ሄክታር  የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ  ከ11 ሺህ በላይ የማንጎ፣ አቡካዶና ብርቱካን ችግኝ መተከሉን አስረድተዋል።

ባለፈው ክረምት በሀይቁ ዙሪያ የተተከሉ 100 ሺህ ለሚሆን ችግኝ እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የተናገሩት  ምክትል ኃላፊው የሀይቁ ዙሪያ  ከእርሻና እንሰሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

በወረዳው የቀበሌ 15  አርሶ አደር ሃድያ አበጋዝ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሀይቁን ከጥፋት ለመታደግ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለሰብል ልማት ብቻ ይጠቀሙበት የነበረውን ማሳቸውን በፍራፍሬ ለማልማት ወስነው  በተያዘው ክረምት ከ200 በላይ የማንጎና አቦካዶ ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል፡፡

"ከተራሮች እየተሸረሸረ የሚወርድ ደለል ወደ ሀይቁ እንዳይገባ በችግኝ ተከላ እየተሳተፍኩ ነው" ያሉት ደግሞ የቀበሌ 12  አርሶ አደር  ጀማል መሐመድ ናቸው።

በሀይቁ ዙሪያ ባላቸው ግማሽ ሄክታር  የእርሻ ማሳ ላይ የፍራፍሬ ችግኝ በመትከል ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

"በሀይቁ አቅራቢያ እንስሳትን ለግጦሽ  ላለማሰማራት ወስኛለሁ" ብዋል ።

መንግስት የሐይቁን ደህንነት ለመጠበቅ የጀመረውን ጥረት በማጠናከር ሀይቁን ለዓሣ ልማትና ለጎብኚዎች  ሊያውለው እንደሚገባ አርሶ አደሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም