ኤጀንሲው የማይንቀሳቀሱ ንብረት የማስተላለፍ ውል አገልግሎቱን ጀመረ

21

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 8/2012 ( ኢዜአ) የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጄንሲ በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጠው የነበረው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የማስተላለፍ ውል አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለወቅታዊ ሥራዎች ቅድሚያ በመሰጠቱ የተቋረጠውን አገልግሎት ዳግም ቀጥሏል።

አገልግሎቱ የተቋረጠው መንግሥት የኪራይ ቅናሽ እንዲደረግ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ የኪራይ ውል እድሳት እንዲሁም የአክሲዮን ማህበራት የቃለ ጉባኤ ምዝገባዎች በወቅቱ ለማከናወን ባስተላለፈው ውሳኔ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በጥናት ላይ በመመስረት ከተቋረጠው አገልግሎት መካከል ዋነኛው የማይንቀሳቀስ ንብረትን በሽያጭም ሆነ በስጦታ የማስተላለፍ ውል አገልግሎት እንደሆነም ገልጸዋል።

ተገልጋዮች አገልግሎቱ በተቋረጠበት ወቅት በኢንተርኔት ማመልከቻዎችን እንዲሞሉ ሲደረግ መቆየቱን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ወቅታዊ የአገልግሎት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው አገልግሎቱ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።

በዚህም  የማይንቀሳቀስ ንብረት ውል ለመፈፀም ያመለከቱ 2 ሺህ ተገልጋዮች በወረፋቸው ቅደም ተከተል እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ይስተናገዳሉ ብለዋል።

ከነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ተገልጋዮች ያለ ወረፋ በመጡበት ጊዜ እንደሚስተናገዱ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተገልጋዮችን አስተናግዶ 522 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የተቋሙ  መረጃ ያሳያል።