የኮቪድ -19 በሽታ መድሃኒት ተብሎ በማዳጋስካር ገበያ ላይ የዋለው መጠጥ የበሽታውን ስርጭት ማስቆም አልቻለም

68

ነሀሴ 8/2020 (ኢዜአ)የኮቪድ 19 በሽታ መድሃኒት ተብሎ በማዳጋስካር በፕሬዝዳንት ገበያ ላይ እንዲውል የተደረገው  ከዕጽዋት የተሰራው መጠጥ የበሽታውን ስርጭት ማስቆም አለ መቻሉ ተገለጸ።

በማዳጋስካር የሚገኙ ሆስፒታሎች የኮቪድ 19 ስርጭት ለመቋቋም ትግል እያደረጉ ቢሆንም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የኮቪድ 19 በሽታን ያድናል ያሉትን ከዕጽዋት የተሰራ መጠጥ እንዲሰራጭ እያደረጉ ይገኛሉ።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከዕጽዋት የተሰራው መጠጥ  በሳይንሳዊ መንገድ ያልተረጋገጠና የአለም የጤና ድርጅት አገራት ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች ጥቅም ላይ እንዳያውሉ ከሰጠው ማስጠንቀቂያ የተጻረረ ነው።

በማዳጋስካር ባለፈው ወር በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአራት እጥፍ ጨምሮ ከ13 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ የ162 ሰዎች ህይወትም አልፏል።

በአገሪቱ  የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ቢሆንም ፕሬዝዳንት አንድሬ ራጆሊና ለቫይረሱ መድሃኒት ነው ያሉትንና ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአገሪቱ በስፋት እየተሰራጨ የሚገኘውን ከተለያዩ ዕጽዋቶች የተሰራው ’ ኮቪድ 19 ኦርጋኒክስ’ የተሰኘውን መጠጥ  እየደገፉ መሆኑ ተጠቅሷል።

‘አርትሚሲያ’ ከተሰኘ ለወባ በሽታ ህክምና ጥቅም ላይ ከዋለ  ዕጽዋትና ከሌሎች በአገሪቱ ከሚበቅሉ ዕጽዋቶች የተዘጋጀው መጠጡ  በማላጋሲ አፕላይድ ሪሰርች ኢንስቲትዩት መመረቱም ተመልክቷል።

በአገሪቱ መጠጡ ለኮቪድ 19 በሽታ መከላከያና መድሃኒትነት ገበያ ላይ መዋሉና ባለፉት አራት ወራት በትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች መቅረቡ ተገልጿል።

በተያዘው ወር መጀመሪያ ላይ ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ዋና ከተማ መጠጡን ጨምሮ የምግብ ሸቀጦችን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ማህበረሰቦች አሰራጭተዋል።

ከተማው ለእንቅስቃሴ ዝግ በሆነበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በመሰብሰባቸው ፕሬዝዳንቱ ላይ ትችት ቢሰነዘርባቸውም  “ ወረርሽኙ ብዙ አይቆይም፤ እያለፈ ነው ፤እናሸንፈዋለን “  ማለታቸው ነው የተገለጸው።

መጠጡ በተሰራጨባቸው በዋና ከተማው አካባቢዎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ አለመሆኑን መናገራቸውም ተጠቅሷል።

ሆኖም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት ሞት በየዕለቱ እየተመዘገበ መሆኑ፣  ሆስፒታሎች በታካሚዎች እየሟሉ እንደሆነና  የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አለም አቀፍ ድጋፍ መጠየቁ በዘገባው ተመልክቷል።

የመጠጡ ፈዋሽነት ላይ ሳይንሳዊ ሙከራ መደረጉ ይፋ ባይደረግም ፤ ምርቱ ለአንዳንዶች ‘የአፍሪካ ኩራት’ ከመባል አላገደውም ። ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራትም ያለ ትራንስፖርት ክፍያ ተሰራጭቷል።

የፕሬዝዳንቱ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ራይናህ ራኮቶማንጋ እንደገለጹት ምርቱን የተጠቀሙና ተጓዳኝ በሽታ የሌለባቸው በርካታ ሰዎች ሙሉ ለመሉ ከኮቪድ 19 በሽታ አገግመዋል።

“ይህ መድሃኒት ስላለን እንኮራለን ፤ እነዚህን መሰል መጠጦች መጠቀም ባህላችን ነው እስከሰራልን ድረስ ክሊኒካዊ ሙከራ አያስፈልገንም “ ማለታቸውም በዘገባው ተገልጿል።

ሆኖም የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር የመጠጡ አጠቃቀም ላይ  ጥንቃቄ የታከለበት አካሄድ ነው የተከተለው ። 

ሆስፒታሎች የኮቪድ ኦርጋኒክስ መሰጠት ያለባቸው የበሽታው ምልክት በአነስተኛ ደረጃ ለሚታይባቸውና የስኳር ህመምና  ሌሎች በሸታዎች ለሌለባቸው ታካሚዎች  መሆን እንደሚኖርበት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም