ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ከዳያስፖራው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች

56

አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2012 (ኢዜአ) በ2012 በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ከላከው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ (ሬሚታንስ) መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 33 ዳያስፖራዎችም ወደ ስራ ገብተዋል ተብሏል።

በተለይ በበለፀጉት አገራት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በታዳጊ አገራት ለሚኖሩ ወገኖቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ለአገር ሲጠቅም ለብዙ ሰዎችም የሕልውና ዋስትና መሆኑ ይነገራል።

የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው እ.አ.አ በ2019 በውጭ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ወደ አገራቸው የላኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) 715 ቢሊዮን ዶላር ነው።

በዚሁ ዓመት በአፍሪካ ናይጀሪያ 23 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቿ ገቢ ስታገኝ ጋና 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ ኬኒያ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን  እንዲሁም ደቡብ ሱዳን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በተለያዩ የዓለም አገራት 5 ሚሊዮን ዜጎቿ እንደሚኖሩ የሚነገርላት ኢትዮጵያም በ2012 በጀት አመት ከዳያስፖራው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር  ገቢ ማግኘቷ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ ሁሉም ሬሚታንስ ተብሎ እንደሚቀመጥ አብራርተዋል።

ኤጀንሲው ከዚህ ውስጥ የዳያስፖራው ወደ አገሩ የላከውን ገንዘብ የመለየት ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ከተላከው 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላሩ ከዳያስፖራዎች የተላከ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በበጀት ዓመቱ የባንክ አካውንት የከፈቱ ዳያስፖራዎች ብዛት 12 ሺህ 661 ሲሆን ከ19 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በተለይም የኢንቨስትመንት አማራጮችንና እድሎችን የማስተዋወቅ ስራ ሲከናወን በመቆየቱ ዳያስፖራው በልማቱ ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት በበጀት ዓመቱ 1 ሺህ 688 በላይ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 33 ዳያስፖራዎች ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።

በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ ዳደርና ድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የተሰማሩ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በትግራይ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ 31 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል።

ከ2 ሺህ 500 በላይ ዳያስፖራዎች በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ መሆናቸውንም ወይዘሮ ሰላማዊት ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ግን የሚላከው ገንዘብና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል ብለዋል።

በቀጣይ የዳያስፖራውን የልማት ተሳትፎ የማሳደግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። 

ከልማት ተሳትፎው ባለፈ የዳያስፖራው መብትን የማስጠበቅ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከናወንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም አገራት ያሏትን ዳያስፖራዎች በአሃዛዊ መረጃ ለማደራጀት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውንም የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እስከ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ድረስ በዳያስፖራው ጉዳይ ማህበራትና ማስተባበሪያ ቢሮዎች እየሰሩ የነበረ ቢሆንም መንግስትን በመወከል የሚሰራ ተቋም አልነበረም።

በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም መብታቸው እንዲጠበቅ ተልዕኮ ተሰጥቶት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በመጋቢት 2011 ዓ.ም ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።