ኢትዮጵያ የዘረመል መመርመሪያ ማዕከል ሊኖራት ነው

181

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የዘረ መል( ዲ-ኤን-ኤ) መመርመሪያ ላብራቶሪ ማዕከል ልትገነባ ነው።

እስካሁን በአገር ውስጥ የዘረ-መል(ዲ. ኤን. ኤ) መመርመሪያ ማዕከል ባለመኖሩ ምርመራዎች ወደ ውጭ አገሮች ይላካሉ።

ማዕከሉ በአገር ውስጥ ሲገነባ ለምርመራ ይወጣ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከተያዘው ዕቅድ አገር አቀፍ ዋና ባዮ ቴክኖሎጂ ላብራቶሪ እንዲኖር ማድረግ አንዱ ነው።

በዚህ ላብራቶሪ ስር የዘረ- መል(ዲ ኤን ኤ) መመርመሪያ ላብራቶሪ  መገንባት ቀጣዩ ተግባር ይሆናል ብለዋል።

ላብራቶሪው የራሱ መስፈርቶች ያሉት በመሆኑ ዘላቂና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መመርመሪያ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ግንባታው በአምስት ዓመታት የሚከናወነው  ላብራቶሪ ፤በአሁኑ ወቅት ቦታውን ለመረከብ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት ዶክተር ካሳሁን፤በተያዘው በጀት ዓመት የዲዛይን ስራዎች እንደሚጀመሩም ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅት እንደ እርሾ የጀመርነው የዘረ-መል ምርመራ አለ" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ   ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ሥራውን ያቀለዋል ብለዋል።

 በተለያዩ ምዕራፎች የሚከናወነው የማዕከሉ ግንባታ፤ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ለማከናወን 400 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ  የዘረ-መል መረጃ ባለቤትን የሚያረጋግጥ ጅን ባንክም በመጥቀስ  ኢትዮጵያ የዲ .ኤን .ኤ .ጅን ባንክ ያስፈልጋታል ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ሰው ዘረመል ምርመራ ካደረገ በኋላ የሚያስቀምጠው ዓለም አቀፍ ጅን ባንክ ማዕከል ውስጥ ነው።

ይህም ለማንኛውም ሰው ክፍት በመሆኑ የባለቤትነት መብት ቢመጣ የመጠየቅ ዕድል እንደማይኖረው ዶክተር ካሳሁን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ያላትን ብዝሃ ህይወት ለምጣኔ ሃብት ጠቀሜታ ከማዋልና ባለቤት ከመሆን እንጻር ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን  አመልክተው፤ በተለያዩ ጊዜያት የተወሰዱ ሃብቶችን ለመጠየቅ ዕድል ይሰጣታልም ብለዋል።

ዲ ኤን ኤ ( Deoxyribonucleic Acid) ትልቅ ሞልዩኪል ሆኖ ህይወት ያላቸውን ማናቸውንም ፍጡራን፣አትክልት፣ እንስሳት፣ባክቴሪያና ሌሎች የዘር-ቀመር (ጄኔቲክ ኮድ) ያዘለ ነው።

የአንድ ፍጡር ዲ ኤን ኤ በዚያ ፍጡር ማናቸውም ህዋስ (ሴል) ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለቤትነቱ የሚረጋገጠው በላብራቶሪ ምርመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም