የአገርና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረግ ሕግ የማስከበር አፈጻጸም ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ተጠያቂ ይሆናሉ-የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

41

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 7/2012 (ኢዜአ) የአገርና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረግ ሕግ የማስከበር አፈጻጸም ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ የፖሊስ ኃይል ለመገንባትም እየተሰራ ስለመሆኑ ኮሚሽኑ ገልጿል።

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ስር የሚገኘውና በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ‘አባዲና’ በሚል ስያሜ የተመሰረተው የዛሬው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከተመሰረተ ከ70 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።

የዕድሜውን ያህል ዕድገት እንዳላሳዬ በብዙዎች ዘንድ የሚነገርለት ይህ ተቋም በአሁኑ ወቅት የፌዴራልና የክልል ፖሊስ መኮንኖችን ተቀብሎ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ድረስ ያስተምራል።

የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አበበ እንዳሉት በተቋሙ ለሁሉም የፖሊስ ሠራዊት አባላት በጥናትን ላይ የተመሰረተ ትምህርትና ስልጠና ይሰጣል።

የስልጠናው ዋና ዓላማም ለአገርና ለዜጎች ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ሕገ መንግስቱና ሌሎች አገራዊ ህጎች እንዳይጣሱ የህግ ማስከበር ተግባራትን ማከናወን መሆኑን ይገልጻሉ።

በዚህም በኮሌጁ በሰላምም ሆነ በአስቸጋሪ ወቅቶች የአገሪቱ ህጎችን ለማስከበር የሚያስችሉ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ነው የተናገሩት።

የፖሊስ ኃይሉ ሕገ መንግስቱና ሌሎች የአገሪቱ ህጎችን፣ የዜጎችና ተቋማትን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ግዴታው እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ፖሊስ የተጣለበትን ኃላፊነት ካልተወጣ ግን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ተቋም ተጠያቂነት እንዳለው ተናግረዋል።

ፖሊስ ወገንተኝነቱ ለህግ ብቻ እንጂ ለማንኛውም ፖለቲካ መወገን ፍጹም አግባብነት እንደሌለው ገልጸው፤ እስካሁን የመጣበት መንገድ ግን ችግሮች የነበሩበት እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ችግሩን በማረም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አያይዘው እንዳሉት ፖሊስ ከኮሌጅ ሰልጥኖ የመለያ ልብስ ለብሶ ሲወጣ ማንኛውንም የወንጀል ሕግና የስነ ስርዓት ህጎች እንዲያስከበር ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነው።

ከተለመዱ የደረቅ ወንጀሎች ውጭ በሆኑ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ከላይ ትዕዛዝ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅውሰው፤ በዚህ ረገድም ቢሆን የመዘግየት ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ይህም ፖሊስ በቂ ዝግጁነት ኖሮት መከላከል የሚችላቸው ችግሮች በተግባር ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት እንደሆነ በቅርቡ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ለአብነት ጠቅሰው ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በዚህም አደረጃት ውስጥ በግለሰብም ሆነ በአመራር ረገድ ለታዩ የአፈጻጸም ክፍተቶች ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ችግሮቹም ከአቅም ማነስ፣ ከልምድና ከሁኔታዎች የሚመነጩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይ እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ በትኩርት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።