ኮሚሽኑ በተለያዩ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች ላይ ጽሁፎችን ላቀረቡ ወጣቶች እውቅና ሰጠ

42

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 7/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች ላይ ጽሁፍ በማቅረብ ለተሳተፉ ከ360 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች እውቅና ሰጠ። 

የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽንና ቲክቫ-ኢትዮጵያ በጋራ በመሆን ወጣቶች በአገራቸው ሰላም ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ፕሮጀክት ቀርጾ ከወራት በፊት ለተሳታፊዎች ይፋ አድርጎ ነበር።

በዚህም በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች ”እኔም የእርቅ ሃሳብ አለኝ ” በሚል ሃሳብ  የተለያዩ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶችን በማጥናትና በመጻፍ ለእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ አቅርበዋል።

ወጣቶቹ ለአገራቸው ሰላም መፍትሄ ለማፈላለግ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የእርቅ ስነ ስርዓቶችን አጥንተው በመጻፍ ላበረከቱት አስትዋጽኦ ዛሬ እውቅናና ምስጋና ተሰጥቷቸዋል

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ዶክተር እዝራ አባተ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ጽሁፎቹ በኮሚሽኑ በኩል ተጨማሪ ጥናት ተደርጎባቸው በቀጣይም በተለያዩ መንገዶች ወደህብረተሰቡ እንዲደርሱ ይደረጋል።

ወጣቶቹ ይህን እንደ መነሻ ወስደው ወደፊት ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ በርካታ ጽሁፎችን መጻፍ እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የቲክቫ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ወጣት በረከት ጉዲሳ በበኩሉ፣ ወጣቶቹ የፕሮጀክቱን ሀሳብ ደግፈውና ጊዜ ሰጥተው በመስራታቸው እውቅና እንደተሰጣቸው ተናግሯል።

“ፕሮጀክቱም ስለሰላም በአንድ ወቅት ብቻ አውርቶ መተው ብቻ ሳይሆን በወጣቶች ውስጥ እንዲሰርጽና ሁሌም እንዲሰሩበት የሚያደርግ ነው” ብሏል።

በባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓት ከጻፉ ወጣቶች መካከል ወጣት ምስጋና ለገሰ ያቀረበችው ጥናታዊ ጽሁፍ በአንድ ብሔረሰብ የእርቅ ስርዓት ላይ ያተኮረ ቢሆንም እንደ አገር የሚጠቅም መሆኑን ተናግራለች።

“ሰላም ለሁሉም ነገር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ሰላም መትጋት አለበት” ብላለች።

ጽሁፍ በማቅረብ የተሳተፈው ሌላው ወጣት ሙልጌታ ወርቅነህ በበኩሉ ስለአገሩ የእርቅ ሃሳብ ማቅረብ የሚችልበት ዕድል በማግኘቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

“በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የእርቅ ስነ ስርዓቶችን በማውጣት ለችግሮቻችን መጠቀም ፋይዳው የጎላ ነው” ያለው ወጣቱ፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ባህላዊ የእርቅ ስነስርአቱ ለአገሪቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

በፕሮጀክቱ 324 ወጣቶች በግል፣ 40 ደግሞ በቡድን በመሆን በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ የእርቅ ስነስርዓቶችን የሚያሳዩ ጽሁፎችን በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ለኮሚሽኑ ማቅረባቸው ታውቋል።