በኮቪድ-19 የተያዙ አባላቱን በራሱ አቅም ህክምና ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

67

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 7/2012 (ኢዜአ) በኮቪድ 19 የተያዙ አባላቱን በራሱ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ህክምና ለመስጠት መዘጋጀቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የእስራዔል ኤምባሲ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብዓቶችን ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዛሬ አበረከቷል።

ከስራቸው ባህሪ አንፃር ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል አንዱ ፖሊስ መሆኑ ይታወቃል።

በፀጥታ ማስከበርና ህዝባዊ ሃላፊነት በስፋት እየተሳተፈ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ 400 የሚሆኑ አባሎቹ ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ቢሆንም የከፋ ህመም እንደሌለባቸውና አብዛኞቹ ማገገማቸውን የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ ተናግረዋል።

እስከ ሁለተኛ ድግሪ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጠው አንጋፋው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ኮቪድ 19 መከሰቱን ተከትሎ በወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በትምህርት ሚኒስትር መመሪያ መሰረት መደበኛ ስልጠናውን ማቋረጡንም ገልጸዋል።

በዚህምን በኢንተርኔት ከሚሰጠው የማስተርስ ትምህርት በስተቀር ትኩረቱን ኮሮናን መካላከል ላይ ባደረጉ አካላዊ አነቅስቃሴ ስልጠናዎች ላይ አተኩሯል ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በቫይረሱ የተጠረጠሩ አባላትን ለማከም ለይቶ ማቆያ የማመቻቸት ስራ መሰራቱን ገልጸው፤  ቫይረሱን ለመከላከል ጥረት ሲደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም ኮሚሽኑ በቫይረሱ የተያዙ አባላቱን በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ውስጥ ህክምና ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡ ከፖሊስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለኮቪድ 19 መከላከያ ግብዓቶችንም ከተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ማግኘቱንና አሁንም ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ገልጸው፣ በዛሬው ዕለትም ከእስራኤል ኤምባሲ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ግብዓቶች ድጋፍ ማግኘቱን ገልጸዋል።

ድጋፉም ከጊዜ ጊዜ ተጋላጭነቱ እየጨመረ በመጣበት ወቅት ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ችረዋል።

ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር በፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ላይ በትብብር እንደምትሰራ ገልጸው፤ ከኮቪድ በፊት የነበረው የትብብር ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በሁለቱም አገራት ፖሊስ ኮሚሽን ፍላጎት እንዳለ ጠቅሰዋል።

ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ተገኘተው ድጋፉን ያበረከቱት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ብሎም ወደ ብልጽግና ለሚደረገው ሽግግር እስራኤል ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

የፖሊስ ሙያ ለኮቪድ 19 ተጋላጭ እንደሚያደርግ በማመንም ለቫይረሱ መከላከያ የሚሆን የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከድጋፍ ርክክቡ በኋላም በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የሚገኘውን የኮቪድ-19 መከላከል ስራዎችና ታሪካዊ ቤተ መዘክር አምባሳደሩ ጎበኝተዋል።