ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

57

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 7/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። 

ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ስምምነትም በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ ዛሬ ተፈርሟል።        

ፕሮጀክቱ “ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሔዎች ለኢትዮጵያ ውሃ መሰረተ ልማት ጥበቃና ማኀበረሰብ አቅም ግንባታ” የሚል መጠሪያም ይዟል።    

ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀትም ተይዞለታል።    

በፕሮጀክቱ ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል የተራቆቱ አካቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ፣ የተለያዩ አገር በቀልና የውጭ አገር ችግኝ ዝርያዎች መትከልና መንከባከብ የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው።   

የውሃ መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም ማኀበረሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም የሚችልበትን አቅም መገንባት ሌላው በፕሮጀክቱ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው።     

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች በተመረጡ ቦታዎች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ነው በስምምነቱ ወቅት የተገለጸው።       

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ አውጥታ ሥራ ጀምራለች።     

በተለይ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አመርቂ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው፣ “ውጥኑ እንዲሳካም አገራዊና ቀጣናዊ ትብብሮች የጎላ ሚና አላቸው” ብለዋል።  

በኢትዮጵያ እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥር ሳቢያ ለማገዶና ሌሎች አገልግሎቶች ደኖች ሲጨፈጨፉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በዚህም ተያያዥ ችግሮች መከሰታቸውን ተናግረዋል።     

በዚህም ምክንያት የመጡ ችግሮችን ለማቃለልና የአየር ንብረት ለውጡን ለመቋቋም ፕሮጀክቱ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በፕሮጀክቱ ሙገር፣ ጉደርና ጀማ ተፋሰሶች በቅድሚያ የሚለሙ ሲሆን፣ ይህም ለሕዳሴ ግድቡ ዘላቂነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።  

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸው በአፍሪካ ከ3 እስከ 5 በመቶ አገራዊ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ) በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደሚታጣ አስታውሰው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ብዙ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  

“የኢትዮጵያ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የአረንጓዴ ልማት ሥራ በአፍሪካ ተጠቃሽ ነው” ያሉት ዋና ጸሐፊዋ “ትልልቅ ጉዳዮች የሚጀመሩት በትንሹ ነው” ሲሉ የዓላማውን ትልቅነት አስረድተዋል።  

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።