ባለስልጣኑ ከ16 ቢሊዮን ቶን በላይ የምግብ እና ምግብ ነክ ጥሬ እቃዎችን ወደአገር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል

156

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 7/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ16 ቢሊዮን ቶን በላይ የምግብ እና የምግብ ነክ ጥሬ እቃዎች ላይ የጥራት ቁጥጥር በማድረግ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

በጉዞ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው እና ገላጭ ጹህፍ የሌላቸው ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ምግቦች በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ እንዳይገቡ ማድረጉንም ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለህጻናት የሚውሉትን ጨምሮ በጠቅላላው 1 ሺህ 998 የሚሆኑ የምግብ አይነቶች አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያስችል ፈቃድ መሰጠቱንም ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ እንዳሉት ባለፈው በጀት ዓመት ከ16 ቢሊዮን ቶን በላይ የምግብ እና ምግብ ነክ ጥሬ እቃዎች ተገቢው የጥራት ቁጥጥር ተደርጎላቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

"በ103 ከተሞች በተደረገ ቅኝት ችግር የተገኘባቸው እንደ ብስኩት፣ ከረሜላ፣ ቸኮሌት፣ አቼቶ፣ ቪንቶ፣ ጨው፣ ማር፣ የለውዝ ቅቤ፣ ዘይት እና የታሸጉ የውሃ ምርቶች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ከአገልግሎት ውጪ ተደርገዋልም" ብለዋል፡፡

ቅቤና ማርን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው ሲሸጡ የነበሩ 13 ተቋማትም መታገዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የጤና ግብአት ቁጥጥርን በተመለከተ የምዝገባ ፈቃድ አገልግሎቱን ላሟሉ 1ሺህ 53 መድኃኒቶችና ለ962 የሕክምና መሳሪያዎች የገበያ ምዝገባ ፈቃድ መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ፣ በዙሪያዋ እና ሌሎች ከተሞችም በተደረገ የስምንት ዙር ቅኝት ህገ-ወጥ መድኃኒት የተገኘባቸው 25 የመድኃኒት ችርቻሪ ድርጅቶች የጽሁፍ፣ የማሸግ እና እገዳ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም አብራርተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተለያዩ ኬላዎች ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ መድኃኒቶች፣ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች እንዲሁም ከ373 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመድኃኒት ጥሬ እቃዎች ተገቢው የጥራት ቁጥጥር ተደርጎላቸው አገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።

በቦሌ አየር ማረፊያ ተገቢ የጥራት ደህንነት ያልተሰጣቸው ከ52 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚገመት የህክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች እና ኮስሞቲክሶችን መያዙንም ተቋሙ አስታውቋል፡፡

ለጤና እጅጉን ጎጂ የሆነና ገላጭ ጹሁፍ የሌለው ከ558 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሲጋራ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መደረጉንም ባለስልጣኑ አመልክቷል፡፡

ለኮሮናቫይረስ ቅድመ መከላከል የሚያግዙ 2 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ግብአቶች የጥራት ደህንነት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንም ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ በ41 ምግብ አምራች፣ በ17 ምግብ አስመጪዎች፣ በ33 የመድኃኒትና ህክምና መገልገያ መሳሪያ ጅምላ አከፋፋዮች እንዲሁም በሁለት የኮስሞቲከስ አምራች ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም