በአማራ ክልል ለ2013 ትምህርት ዘመን የዝግጅት ስራ እየተካሄደ ነው

112

ባህርዳር ነሓሴ 7 /2012 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል በ2013 የትምህርት ዘመን ከ6 ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። 

ቢሮው በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ከዞንና ከተማ አስተዳደሮች ከተወጣጡ  የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ባህርዳር ላይ እየተወያየ ነው።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ በውይይት መድረኩ እንደገለጹት በ2013 የትምህርት ዘመን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ቅድመ ዝግጅቱ ኮሮናን ታሳቢ በማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር በሚወርደው አቅጣጫ መሰረት ከ6 ሚሊዮን በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በመመዝገብ ተቀብሎ ለማስተናገድ  መሆኑን አስረድተዋል።

በነባርና አዲስ እየተገኑቡ በሚገኙ ከ9ሺህ በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችን የመጠገን ፣ የማጽዳትና የውስጥ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለመማር ማስተማር ስራ የሚያግዙ መፃህፍት የማመቻቸት ስራም እንዲሁ።

"ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ተማሪዎችና መምህራን ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በየትምህርት ቤቶች እንዲሟሉ ይደረጋል" ብለዋል።

ለስምንተኛና 12 ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር በሚያሳውቀው ቀን የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ለፈተና እንዲቀርቡ የሚያስችል መሰናዶ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል ።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ዜና ገብረማርያም በበኩላቸው በአዲሱ የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ምቹ፣ ፅዱና ሳቢ ለማድረግ ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ከ30 በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በነባር ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችን የመጠገን፣ ቁሳቁስ የማሟላትና  ተጓዳኝ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል ።

 "የምዝገባ ጊዜ ባይወሰንም  ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወን እንገኛለን" ያሉት ደግሞ  የጎንደር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ወንድማገኝም ናቸው።

በተለይም ተማሪዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ  በመጠበቅ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል የቁሳቁስ አቅርቦትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል ።

በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው ውይይት የ2013 የትምህርት እቅድና ዝግጅት ዙሪያ  ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም