የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሲያካሄዱት የቆየው ኮንፍረንስ ተጠናቀቀ

96

ባህር ዳር ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሄዱት የቆየው ኮንፍረንስ መጠናቀቁን የፓርቲው ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ማምሻውን በሰጡት መግለጫ  በኮንፈርንሱ የተሳተፉት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በለውጡ ዙሪያ መክሯል ብለዋል።

በማህበራዊ ፣  ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውጤታማ መሆን የህግ የበላይነት የቅድሚያ አጀንዳ ሆኖ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ስለተከናወኑት ስራዎች በኮንፍረንሱ  መገምገማቸውን ገልፀዋል።

በተከናውኑት ስራዎች በተለይም በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ህዝብን ያውኩ የነበሩ ቡድኖችን በማስተካከል ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር መቻሉ በበጎ ጎኑ መነሳቱን ጠቅሰዋል።

ወቅታዊ የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል የልማት ስራዎቹ ሳይደናቀፉ እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ በቫይረሱ ምክንያት ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡና የምርመራ ጣቢያዎችን በማሳደግ የተከናወኑ ስራዎችም እንዲሁ መልካም እንደሆኑ ተመላክተዋል።

በክረምቱ የመኸር እርሻና የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን በተደራጀ አግባብ መሰራቱ የተሻለ ውጤት እንዲመዘግብ እንዳስቻለ መወሳቱንም ገልጸዋል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ተከትሎ ሀዘናቸውን ለመግለጽ የወጡ ሰዎችን ሽፋን በማድረግ በሌሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት በኮንፍረንሱ  መድረክ መወገዙንም  አስታውቀዋል።

ድርጊቱ በጽንፈኞች ትህነግና ኦነግ ሸኔ አቀነባባሪነት የተከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ አገኘሁ ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ  በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የከፍተኛ አመራሩ ኮንፈረንስ በሙሉ መግባባት መካሄዱን  ያስታወቁት ኃላፊው መከፋፈል አለ ተብሎ የሚነዛው ወሬም ከእውነት የራቀና የትህነግ አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይ በለውጡ ሂደት ፣ ኮሮናን በመከላከል፣ የክረምት ስራዎችና ሌሎች ወቅታዊ ተግባራት ዙሪያ እስካሁን የተከናወኑት እንዳሉ ሆኖ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ተለይተው  አቅጣጫ በማስቀመጥ የኮንፈረንሱ መረሃ ግብር  መጠናቀቁን አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል።