እነ እስክንድር ነጋ 'መከራከር አንፈልግም' ሲሉ ጠበቆቻቸውን አሰናበቱ

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2012(ኢዜአ) በወንጀል ጉዳይ የተጠረጠሩት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና ወይዘሮ ቀለብ ስዩም 'መከራከር አንፈልግም' ሲሉ ጠበቆቻቸውን አሰናበቱ። 

በወንጀል ጉዳይ በተጠረጠሩት እነ እስክንድር ነጋ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ በተያዘው ቀጠሮ መሰረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ቁጥር 215730 የቀረቡት ተጠርጣሪዎች አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና ወይዘሮ ቀለብ ስዩም ጠበቆች የዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ላይ ባለ ሁለት ገጽ አስተያየት አቅርበዋል።

በአስተያየታቸውም በቀዳሚ ምርመራ ላይ ዐቃቤ ህግ ካቀረባቸው ሰባት ምስክሮች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ማንነታቸው ሳይታወቅ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩለት እንዲሁም ከ4ኛ እስከ 7ኛ ያሉት ምስክሮች ደግሞ በዝግ ችሎት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ምስክሮች ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቁ ስለመሆናቸው ማስረጃ አልቀረበም በሚል የዐቃቤ ህግ አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ጠበቆች ባቀረቡት አስተያየት ላይ ምላሽ እንዲሰጥ የተጠየቀው ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ምስክሮች የደህንነት ስጋት ያለባቸው መሆኑን አቤቱታ እንዳቀረቡለት ገልጿል።

ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ያሉ ቢሆንም ወንጀል የተፈጸመው በተደራጀ ቡድን በመሆኑ በምስክሮቹ ላይ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎች የመከራከር መብት እንዳላቸው ሁሉ ምስክሮችም የመኖር መብታቸው ሊነካ እንደማይችል ከግምት ውስጥ እንዲገባለት ዐቃቤ ህግ ጠይቋል።

''የሚካሄደው የቀዳሚ ምርመራ የተጠርጣሪዎችን የመከላከል መብት የሚጎዳ አይደለም'' ያለው ዐቃቤ ሕግ፤ ያቀረባቸው የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች እንዲሰሙለት ጠይቋል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ የቀዳሚ ምርመራ የሚካሄደው በዋናነት ማስረጃን ጠብቆ ለማቆየት በመሆኑ ከዚህ በፊት ብይን በሰጠበት አግባብ የምስክሮች ቃል ከመጋረጃ ጀርባና በዝግ ችሎት እንዲካሄድ በይኗል።

''ክሱ ለተጠርጣሪዎች ሊደርሳቸው ይገባል'' በሚል የቀረበው አስተያየት የተመሰረተ ክስ ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም።

ምስክሮች ሲሰሙ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ዋና ጥያቄ፣ መስቀለኛ ጥያቄና ቀዳሚ ጥያቄ በመጠየቅ ምስክሮችን የመፈተን መብት እንዳላቸው ገልጿል።

የቀረበው ማስረጃ የሚመረመረው በከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ የቀዳሚ ምርመራ ምስክርነት ከመጋረጃ ጀርባ እና በዝግ ችሎት መሰማቱ ተጽዕኖ የሌለው በመሆኑ በዚሁ አግባብ እንዲሰማ ብይን ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ 5ኛ እና 6ኛ ምስክር አቅርቦ ሊያሰማ የነበረ ቢሆንም ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል ከባድ በመሆኑ ሂደቱ በግልጽ ችሎት መታየት እንዳለበት በመግለጽ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ እስክንድር ''በግልጽ ችሎት ጉዳዩ ካልታየ መከራከር ስለማንፈልግ ጠበቆቻችንን አሰናብተናል'' ብለዋል።

በችሎቱ መገኘት የማይፈልጉ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ''ወደ ማረፊያ ገብተን በሌለንበት መታየት አለብን'' ሲሉ ተናግረዋል።

2ኛና 3ኛ ተጠርጣሪም ተመሳሳይ ሃሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ጠበቆች በበኩላቸው የጥብቅና አገልግሎት በውል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ደንበኛው ውሉን እንዳፈረሰ ከገለጸ ጥብቅና መስጠት እንደማይችሉ በመግለጽ፤ ፍርድ ቤቱ ይህን ተገንዝቦ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የተጠየቀው ዐቃቤ ሕግ የተጠርጣሪዎችን መብት እየጠበቀ ፍርድ ቤቱ አግባብ ባለው ሁኔታ በተከላካይ ጠበቃ ክርክሩ መካሄድ እንዳለበት ገልጿል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ ተጠርጣሪዎች በጠበቃ መከራከር እንደማይፈልጉ ያቀረቡትን ሃሳብ መርምሮ 'ጠበቆች ተጠርጣሪዎች ካልፈለጉ የመወከል መብት የለንም' በማለታቸው አሰናብቷቸዋል።

ለተጠርጣሪዎች ተከራካሪ ጠበቃ በፍርድ ቤት ሬጅስትራር በኩል እንዲመደብላቸውና የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች እንዲሰሙ ለነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ይዞ እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም