በወላይታ ዞን ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሱ ተገለጸ

66

ሀዋሳ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) – በወላይታ ዞን ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ አሁን ላይ ወደ አንጻራዊ ሰላም መመለሱን የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያጣራ የሰጠው መግለጫ ስሀተት መሆኑን አመልከተዋል።

ኃላፊው ለኢዜአ እንደተናገሩት የተወሰኑ የወላይታ ዞን አመራሮች ሕዝቡ የጠየቀውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ከአሰራር ውጭ በሌላ አቅጣጫ ለመምራት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከሁለት ቀናት በፊት እነዚሁ አመራሮች በሕገወጥ መንገድ ከተደራጁ ቡድኖች ጋር  ስብሰባ ሲያካሂዱ በክልሉ ኮማንድ ፖስት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ገልጸዋል።

በወቅቱ ከተከሰተው ችግሩ ጋር በተያያዘ የዞኑ አመራሮችን ጨምሮ 24 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተው ከጉዳይ ጋር ተሳትፎ የሌላቸውና በወቅቱ ስብሰባው ላይ ተገኝተው የነበሩ የሀገር ሽማግሌዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች ተጣርቶ እንዲፈቱ ተደርጓል ብለዋል።

የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎም አመራሮችና ሕገወጥ ኃይሎች ያደራጇቸው ቡድኖች በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች መንገድ መዝጋት በተለይ ቦዲቲና ሶዶ ከተሞች ላይ ሁከት በመፍጠር በአካባቢው አለመረጋጋት እንዲሰፍን እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

መንገድ በመዝጋትና ሁከት በመፍጠር ላይ የነበሩ ቡድኖች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በፈጠሩት ችግር  የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸው 15 ሰዎች ላይ ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው አሰረድተዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ባደረገው ጥረት በዞኑ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር  በመቆጣጠር አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን  መቻሉን ገልጸዋል።

ስለተወሰደው እርምጃ ለሕዝቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የአደረጃጀት ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ ከሕዝቡ ጋር በመምከር ላይ እንደሆኑም አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል በሕወሐት የሚመራው ድምፀ ወያኔና በአቶ ጃዋር የተቋቋመው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሕዝቡ ጥያቄ ወደሌላ አቅጣጫ እንዲያመራና አካባቢው ላይ ትርምስ እንዲፈጠር በአካባቢው ወኪል በመመደብ ጭምር ሲያራግቡ እንደነበርም አውስተዋል።

አሁንም ቢሆን የወላይታ ሕዝብ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጽኑ አቋም አለው ያሉት አቶ ዓለማየሁ አመራሩም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መግባባት ከፈጠረ በኋላ ከአቋሙ በመንሸራተት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ አጀንዳ ለማረማድ ጥረት ማድረጉን አስራደተዋል።

በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች ሕዝብ ያነሳቸው ጥያቄዎች ሕግን፣ ፍትሐዊነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት አድርገው እየተመለሱ እንደሆነ ጠቁመው ቀሪ ጉዳዮችም በሰከነ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ከሕዝቦች ጋር መግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል።

ሌሎች አካባቢዎች ላይም ቢሆን ተመሣሣይ ድርጊት ውስጥ ገብተው በሚገኙ አመራሮች ላይ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያጠራ የሰጠው  መግለጫ ስህተት መሆኑን የክልሉ መንግሥት ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን  አቶ አለማየሁ አመልክተዋል።