አስተዳደሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አገኘ

51

አዲስ አበባ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የሚከላከልበት ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተረከበ።

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመከላከል ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

ወረርሽኙን  ለመከላከል በግንባር ቀደምነት የተሰለፈውን የጤና ባለሙያዎች በግብዓቶች፤ ወረርሽኙን ባስከለተለው ቀውስ ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን ደግሞ በቀለብና የንጽሕና መጠበቂያዎችን ለማሟላት ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል። 

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አምስት ድርጅቶች ያበረከቱትን ድጋፍ ዛሬ ተረክበዋል።

ምክትል ከንቲባው በዚህ ወቅት እንደገለጹት የበሽታው ሥርጭት እየሰፋ ባለበት በዚህ ወቅት ድርጅቶቹ ላደረጉት ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል። 

ድጋፉ በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚታየውን ችግር እንደሚያቃልለው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ወረርሽኙ  በተለይ በመዲናዋ እየጨመረና ሕይወት እየቀጠፈ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በመተግበር ሥርጭቱን ለመግታት ጥረት እንዲያደርግ  አሳስበዋል። 

የከተማዋ ነዋሪዎች ራሳቸውን ከወረርሽኙ ከመጠበቅ በተጨማሪ ልማቱን እንዲያስቀጥሉ ኢንጂነር ታከለ አስገንዝበዋል።

ድጋፉን ከሰጡት መካከል ባኮማል ኢንጂነሪንግ የተሰኘ ድርጅት ለ200 ሰዎች የሚያገለግል የኦክስጅን ኮንሰንትሬተር መሣሪያ ሰጥቷል።

መሣሪያው በቀን ለ200 ሰዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተገልጿል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩ ኤስ ኤይድ) ለ4 ሺህ 429 አባወራዎች ድጋፍ  የሚሆን 26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለግሷል።

ድጋፉ ለሦስት ወራት የሚሰጥ ሲሆን፤ በወር ለአንድ አባወራ ሁለት ሺህ ብር እንደሚከፋፈል ተመልክቷል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 26 ካርቶን ሣሙና፣ 500 አንሶላ፣ 300 ፍራሽና የግንባታ ቁሳቁስ አበርክቷል።

ቤዛ ራይድ የ100 ሺህ ብር ድጋፍ  ሲሰጥ በርኪ ቴክኖሎጂ ደግሞ ከአሚኦ ኢንጂነሪንግ ፒ.ኤል.ሲ ጋር በመተባበር  75 ሺህ ብር ግምት ያለው የፀረ-ባክቴሪያ ኬሚካል መርጫ ለአስተዳደሩ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም