የጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ለዶሮ እርባታ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ ቤቶችን ሠርቶ አስረከበ

102

አዲስ አበባ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) - የጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ለዶሮ እርባታ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ ቤቶችን ሰርቶ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ሴቶች አስረከበ። 

በክፍለ ከተማው ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ  የተቋቋመው የምዕራፍ ሁለገብ  የከተማ  ልማት ድርጅት በኮሌጁ የተሰሩትን ቤቶች ተረክቧል።

ለእያንዳንዱ የዶሮ ቤት መሥሪያ 6 ሺህ 500 ብር ወጪ መደረጉ ተገልጿል።

የኮሌጁ ዲን አቶ ፀጋዬ አዱኛ እንደተናገሩት፤ የተዘጋጁት የዶሮ ቤቶች ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው።

ቤቶቹ እያንዳንዳቸው  60 ዶሮ መያዝ የሚችሉ ሲሆን  ምቹነት ያላቸው እንደሆኑ  ጠቁመዋል።

ኮሌጁ  ከተሰጠው ተግባር በተጨማሪ በክፍለ ከተማው የሚገኙ  ሥራአጥ  ወጣቶችን  በማሰልጠን  ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ተግባር  እያከናወነ እንደሚገኝ  የተናገሩት  አቶ ፀጋዬ፤ ከጥቅም ውጪ የሆኑ የከተማ አውቶብሶችን በማደስ ለአገልግሎት  ማብቃቱን  ገልጸዋል።

በኮሌጁ የፈርኒቸር ሥራዎች ክፍል ኃላፊ አቶ ሸረፈዲን ከሚል በበኩላቸው የዶሮ ቤቶቹ  በብረት ከሚሰራው የዶሮ ቤት አንጻር ምቹነት ያለው እንደሆነ አመልክተዋል።

በብረት የሚሰሩት በሙቀት ወቅት እጅግ የሚሞቁ፤ በቅዝቃዜ ወቅትም በተመሳሳይ ቀዝቃዛ በመሆናቸው ለዶሮ እርባታ ምቹነት እንደሌላቸው ገልጸው፤ ከእንጨት የተዘጋጀው ቤት ይህንን ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቤቱን ለማንቀሳቀስና በተመጣጣኝ ወጪ ለማዘጋጀት ከብረት እንጨት ተመራጭ መሆኑን አመልክተዋል።

የዶሮ ቤቶቹን የተረከቡት የምዕራፍ ሁለገብ የከተማ ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ  ወይዘሮ ትዕግስት አየለ ምቹ የዶሮ ቤት ቢዘጋጅም ብዙዎቹ ተደራጅተው ያሉት ሴቶች ተከራዮች በመሆናቸው የቦታ ችግር እንደሚገጥማቸው ጠቁመዋል።

በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ  መኮንን  የቦታውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ ሴቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ ሲገቡ የመሥሪያ ቦታ ሼድ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አሁን የዶሮ ቤቶቹን የሚያገኙት ሴቶች ለዶሮ እርባታ በተዘጋጁ ሼዶች ውስጥ ባሉ ክፍት ቦታዎች እንዲገቡ የሚመቻች መሆኑን ጠቁመዋል።

የዕድሉ ተጠቃሚ  የሆኑት ወይዘሮ ታደለች  ኃይሉ ኮሌጁ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ የዶሮ ቤት ሰርቶ መስጠቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም