የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለአቅመ ደካሞች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

138

አዲስ አበባ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ነዋሪዎች በኮሮና ወረረሽኝ ሳቢያ ገቢያቸው ለቀነሰ አቅመ ደካሞች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲውል የ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ቦንድ ገዝተዋል።

የድጋፉ አስተባባሪ አቶ ወንድሙ ግዛው "የአካባቢው ወጣቶችን በማስተባበር ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ስኬታማ ሥራ ሰርተናል" ብለዋል።

ወጣቶቹ የአካባቢያቸውን ፀጥታ ከማስከበር ጀምሮ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የወረዳውን ነዋሪዎች በማስተባበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ወረዳው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ሀብት በማሰባሰብ ላከናወነው ሥራ አመስግነዋል።

ነዋሪዎቹ ያደረጉት ድጋፍ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ያግዛል ብለዋል።

ወረርሽኙ እንዳይባባስም መንግሥት ያወጣቸውን መመሪያዎች እንዲተገብራቸው ኃላፊው ነዋሪዎችን ጠይቀዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ አፍራሳ በበኩላቸው ነዋሪዎቹ ወገንን ለመደገፍ ያደረጉት ድጋፍ አርአያነት እንዳለው ተናግረዋል።

ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ እየታየ ያለው መዘናጋትን በማስወገድ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የአካባቢው ወጣቶች “የሚተካውን ደም በመስጠት የማይተካውን ሕይወት እናድን!” በሚል መሪ ቃል የደም ልገሳ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም