የኃይማኖት አባቶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

32

ነቀምቴ ነሐሴ 06/2012 (ኢዜአ) በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የኃይማኖት አባቶች የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ ፡፡

የከተማ  የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል  አቶ ምስጋኑ ወጋሪ ዛሬ በከተማው ከሚገኙ የኃይማኖት አባቶች ጋር  በበሽታው መከላከል ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ  በተፈጠረው  መዘናጋት የበሽታው ስርጭት አሳሰቢ ሆኗል፡፡

በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት በማስቀረት ወረርሽኙን ለመግታት በሚደረገው ጥረት  የኃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም በየእምነት ቤቶቻቸው፣ በሕዝቡ መካከል በመግባት ጭምር እየቀሰቀሱ በማስተማር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በመቀናጀት  እንደሰሩም አመልክተዋል።

የነቀምቴ “ወልዳ ቡርቃን ነጋ ኢየሱስ” ቤተ እምነት አገልጋይ ወንጌላዊ ባጫ ቅናጢ በሰጡት አስተያየት ቤተ እምነታቸው ኮሮናን ለመከላከል መንግሥት ያወጣውን  አዋጅ በመከተል ተከታዮቻቸውን ለማስተማር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።፡

በከተማ አስተዳደሩ የጠየቀውን  ትብብር በአግባቡ  ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ በሽታውን ለመከላከል  የተቋቋመው ግብረ ኃይል  ክፍተት ስላለበት  ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የጨለለቂ ቡርቃ ጋሪ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ አሰፋ ተመስጌን በበኩላቸው በአካባቢው  ተጀምሮ የነበረው  በየቦታው የእጅ መታጠብና አካላዊ ርቀት መጠበቅ ለተወሰኑ ሳምንታት ቆይቶ   አሁን  መዘንጋቱን ተናግረዋል።

ከተፈጠረው መዘናጋት ጋር ተያይዞ በሽታው አሳሰቢ ስጋት መሆኑን ጠቁመው  ቤተ እምነታቸው አሁንም ቢሆን አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ምዕመናን እጃቸውን ሳይታጠቡ፣ የፊትና አፍንጫ  ጭንብል ሳያደርጉና አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ እንደማይስናገዱ አስረድተዋል፡፡

እንደ ኃይማኖት አባትነታቸውም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት የዜጎችን ሕይወት ለማዳን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ባጃጆች፣ ሞተር ብስክሌቶች ፣ ሚኒ ባስ አሽከርካሪዎች  ሰውን በሰው ላይ እየጫኑ ከታሪፍ በላይ ከማስከፈላቸውም በላይ ለበሽታው ስርጭት መንስኤ  በመሆናቸው  ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።

በየቤተ እምነታቸውና ከቤተ እምነት ውጭም ሕዝቡን በማስተማር መንግሥት ያወጣውን አዋጅ በተግባር በመተርጎም ህዝቡ ራሱን ከበሽታው  እንዲጠብቅ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የነቀምቴ ቅዱስ ገብረኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ አባ ገብረ ሥላሴ መኮንን ናቸው።

የነቀምቴ የፈትህ መስጊድ የኃይማኖት አባት አቶ መሐመድ አደም በበኩላቸው  ሕዝቡ አሁን ከገባበት መዘናጋት በመውጣት ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ  በሚኖሩበት አካባቢ ሕብረተሰቡን በማስተማር ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ  ከግብረ ኃይሉ ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ደሣለኝ ቀናቴ  ከኃይማት አባቶች ያቀረቡትን ቅሬታ እንደ ግብዓት በመውሰድ የተፈጠሩትን ክፍተቶች ለማስተካከል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኃይማኖት አባቶችም  በሽታውን ለመከላከል የተደነገገውን  አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር “የተቋቋመው ግብረ ኃይል  የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም” በማለት የተሰማቸውን ቅሬታ አሰምተዋል፡፡