የትምህርት ሚኒስቴር 2ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አከናወነ

53

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 6/2012 ( ኢዜአ) የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄዱ።

በአይ ሲ ቲ ፓርክ የተካሄደው መርሃ ግብር በሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተከሉት 500 ሚሊዮን ችግኞች አካል ነው።

በሚኒስቴሩ በመርሃ ግብሩ ለመትከል ከታቀዱ 24 ሺህ ችግኞች መካከል እስካሁን 21 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ  ዕቅዱ እስኪሟላ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብና ለተፈለገው ዓላማ ለማብቃት በሶስት ወራት እንክብካቤ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ 500 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ድረስ ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በመርሐ ግብሩ በባለቤትነት መንፈስ በመሳተፍ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን፤መንከባከብ ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘንድሮ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል የተያዘው ዕቅድ ሙሉ በሙሉ መሳካቱን ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ አስታውቀዋል።

ከመጪው ዓመት ጀምሮ ጎረቤት አገሮችም በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደሚሳተፉም ዶክተር ዓቢይ በባህር ዳር በተካሄደ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።