የኢትዮ ኤርትራ ህዝቦች ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የዛላ አንበሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

124
መቀሌ ሃምሌ 4/2010 የኢትዮ ኤርትራ ህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በዛላ አንበሳ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት  መመለስ  ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ከሀያ ዓመታት በኋላ በአስመራ ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱም ህዝቦች ሰላም ለማምጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ዛላ አንበሳ ከተማ ዙሪያ ከኤርትራ በድንበር ከሚጋሩ ቀበሌዎች  ውስጥ የማርታ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  አንዱ ነው፡ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር  ተስፋዬ ገዛኸኝ በሰጡት አስተያየት  ሰላም ለማምጣት በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ከኤርትራ ወንድም ህዝብ ጋር በሀዘን ፣በደስታና በሌሎችም የነበራቸውን ማህበራዊ ግንኙነት ለማስቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ "በድንበር ግጭት ምክንያት ላለፉት ዓመታት ከወንድሞቻቸውና ልጆቻችት  ተለያይተን  ኖረናል"ያሉት ደግሞ የቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ነዋሪ አርሶ አደር ታደሰ ማርቆስ ናቸው፡፡ ተቋርጦ  የቆየውን ማህበራዊ ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለሱ  ለሁለቱም ህዝቦች ዘላቂ ሰላም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው የድንበሩን ጉዳይ እልባት ለመስጠት በሚካሄደው አፈጻጸም ላይ ከሁለቱም ሀገራት የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ማሳተፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የዛላ አንበሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ጠዓመ ለምለም በበኩላቸው ላለፉት  ዓመታት ሰላምም ጦርነትም የሌለበት አስቸጋሪ ሁኔታ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በድንበር ላይ የሚገኙ  ሁለቱም ህዝቦች ግንኙነታቸው  አሜሪካ ውስጥ ከሚገኙ ቤተሰቦች አማካኝነት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው  አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱም ህዝቦች ሰላም ለማምጣት የጀመሩት ጥረት ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ይመለሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ወይዘሮ አምለሰት ተስፋዬ የተባሉ የከተማው ነዋሪ  የሰላም ድርድሩ ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መልኩ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ተናግረው "በድንበር ይገባኛል ምክንያት በተፈጠረው ግጭት ወንድሞቻችን ገብረናል፤ ከእንግዲህ በኋላ ልጆቻችን መገበር አንፈልግም" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም