በአማራ ክልል ለህዳሴ ግድብ የ3 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ተከናወነ

78

ባህርዳር ነሐሴ 6/ 2012 (ኢዜአ ) በአማራ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ ምክንያት  በሐምሌ ወር ብቻ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀሙ ተገለጸ።

የውሃ ሙሌቱ በመጠናቀቁ  በተፈጠረው መነቃቃት   በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም  ብቻ  ከቦንድ ሽያጭ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን  በክልሉ  ህዳሴ ግድብ  ህዝባዊ  ተሳትፎ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኘ አበበ ተናግረዋል፡፡

 በቦንድ ግዥው ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሃብቶች፣ ጨምሮ የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት መሳተፋቸውን  አቶ ተናኘ ጠቅሰዋል።

 የክልሉ ህዝብ ግድቡ ለፍፃሜ እንዲበቃ ከ50 ብር ጀምሮ የአቅሙን ያህል ቦንድ በመግዛትና በ"8100 A "ብሎ በመላክ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡

በባህርዳር ከተማ  ነዋሪ የሆኑት   አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ በሰጡት  አስተያየት እስካሁን  የሁለት ወር ደመወዛቸውን ለህዳሴው ግድብ የቦንድ ግዥ በማዋል በግንባታው ላይ አሻራቸውን ማኖራቸውን ገልፀው  በቀጣይም አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ  ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የ7 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን የተናገሩት ደግሞ  ሌላው የከተማው ነዋሪ የመንግስት ሰራተኛ አቶ ደሴ ገላው ናቸው።

 አቶ ደሴ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ተከትሎ  ለሶስተኛ ጊዜ የአንድ ወር  ደመወዛቸውን በዓመት ከፍለው ለመጨረስ የ8 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ ለመፈፀም እንደተዘጋጁም ገልጸዋል።

በክልሉ በ2012 የበጀት ዓመት ህብረተሰቡ ለህዳሴው ግድብ ባደረገው የቦንድ ግዥና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተሳትፎ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት አስተዋጾኦ  መደረጉን ከህዝባዊ ተሳትፎ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽህፈት የተገኘው  መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም