የትግራይ ሕዝብ የፈለገውን መገናኛ ብዙኃን እንዳይከታተል ተደርጓል-- የትግራይ ክልል ተወላጆች

78

አዲስ አበባ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) የትግራይ ክልል ሕዝብ የፈለገውን መገናኛ ብዙኃን እንኳን እንዳይከታተል ጫና እየተደረገበት መሆኑን በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ተናገሩ።

ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ከአጎራባች ክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለማጋጨት የሚያደርገውን የሴራ ፖለቲካ እንዲያቆም ጠይቀዋል።

ተወላጆቹ ዛሬ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የትግራይ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት መድረክ በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት ክልሉን የሚመራው አፋኝ ቡድን ሕዝቡን የመረጠውን መገናኛ ብዙኃን እንኳን ለመከታተል ዕድል ነፍጎታል።

የክፍለ ከተማው ነዋሪ የወይዘሮ ፅጌረዳ ተስፋዬ  "ሕወሓት መቀሌ ላይ ከመሸገ ጀምሮ የክልሉ ሕዝቦች በነፃነት እየኖሩ አይደለም።"

የክልሉ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት መስዋዕትነት ቢከፍልም፤ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ከወገኖቹ እንዲነጠል ጫና እየተደረገበት ነው ብለዋል።

በዜጎች ላይ የሚደረገው ጫና ከክልሉ የመገናኛ ብዙኃን ውጭ አገራዊ ሥርጭት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን  ለመከታተል እንደሚቸገር ተናግረዋል።

ሕዝቡ በፌደራል መንግሥትና በአጎራባች ክልል ሕዝቦች ላይ ጥላቻ እንዲያድርበትና የመነጠል ስሜትን የሚያንፀባርቁ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳዎች መቆም አለባቸው ብለዋል።

በትግራይ ውስጥ ከሕወሓት ሀሳብ ውጭ ለሚንቀሳቀሱ የክልሉ ዜጎች ''ባንዳ'' የሚባል ሥም መሰጠቱ አግባብ አይደለም ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ለምለም ሣሙዔል የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

"ባንዳ የሚለው ቃል አገርን ለሸጠ ወይም አገርን ለከዳ ነው" የሚሰጥ ነው ያሉትአስተያየት ሰጪዋ የሕወሓትን ሀሳብ የሚቃወሙ ዜጎችን እንደ ጠላት መፈረጁ አምባገነንነቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

አቶ ብሩክ አስናቀ የተባሉ የክልሉ ተወላጅ በበኩላቸው ሕወሓት ከለውጥ በኋላ ያለውን መንግሥት አሃዳዊ ነው ብሎ የሚፈረጀው ለራሱ ጥቅም እንጂ፤ ለሕዝቡ አስቦ አይደለም ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ መስዋዕትነት የተከፈለለትን የዴሞክራሲያዊት አገር ግንባታ መቀላቀል ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል።

ልዩነቶችን በውይይት የሚፈቱበትት ሥርዓት እያለ ሕዝቡን ዳግም ወደ ጦርነት ከሚያስገባ እንቅስቃሴ እንዲገታ ጠይቀዋል።

ሕወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥት ኢትዮጵያን ከሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ጋር በፈጠረው የፖለቲካ አቋም ልዩነት የአገርና የሕዝብ አንድነት የሚነጥሉ ተግባራት እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም