በባሌ ዞን በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 114 ቤተሰቦች ተፈናቀሉ

73

ጎባ ኢዜአ ነሐሴ 6/2012 በባሌ ዞን የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ 114 ቤተሰቦች መፈናቀላቸውንና በ1ሺህ 600 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል መውደሙን የዞኑ የአደጋ ስጋት አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብረሃም ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  ጉዳቱ የደረሰው ላለፉት ተከታታይ ቀናት እየጣለ ባለው በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ  ነው፡፡

በዞኑ የሲናና እና ጎባ ወረዳዎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ 114 ቤተሰቦችን ከቤት ንብረታቸው ሲያፈናቅል፤  በ1ሺህ 600 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ ሰብልና አረንጓዴ መስኮች መውደማቸውን አሰታውቀዋል።

በጎርፉ ምክንያት የተፈናቀሉ ቤተሰቦች በአካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲጠለሉ መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፤ ለተፈናቃዮቹ የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የጣለውን ከባድ ዝናብ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ማስተንፈሻ ቦይ በመክፈት፣ የመገደብና ውሀውን ከማሳ የማስወጣት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።

ኃላፊው እንዳሉት፤ የሚቲዎሮሎጂ  ትንበያ እንደሚያሳያው ዝናቡ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በየደረጃው የተቋቋሙ የአደጋ ተከላካይ  ግብረ ኃይሎች መልክት ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።

ግብረ ሃይሉ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው አስታውቀዋል።

በአደጋው ተጎጂ የሆኑ ቤተሰቦችን ለማቋቋም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የሲናና ወረዳ የአደጋ ስጋት አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙክታር ኡስማን ናቸው፡፡

ከወረዳው  ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አስቴር ወርቁ እንዳሉት፤ ድንገተኛ ጎርፍ ባስከተለው አደጋ በማሳ ላይ የዘሩትና ለእለት ጉርስ የሚሆናቸውም ሳይቀር በጎርፉ በመወሰዱ ለችግር ተጋልጠዋል፡፡

መንግስት በተደጋጋሚ ለሚያጠቃቸው የጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመቻችላቸው የጠየቁት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ  ነዋሪ አቶ ሀሰን ከማል ናቸው፡፡

በጎርፍ አደጋው የደረሰው ጉዳት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ከዞኑ የአደጋ ስጋት አመራር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ የመለክታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም