የህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያዊያን ሊረባረቡ ይገባል-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

91

ባህር ዳር፣ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በማበልጸግ የህዝቦቿን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ መላ ኢትዮጵያዊያን ሊረባረቡ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።

ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል መረሃ ግብር የማጠቃለያ ፕሮግራም ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

በፕሮግራሙ ስነሰርዓት ችግኝ በመትከል የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ሲመጣ የገባውን ቃል ለመፈፀም ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከልም በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞዋ በደን የተሸፈነች እንድትሆን ማድረግ ነው ብለዋል።

ከደን መራቆት ጋር ተያይዞ የሚከሰትን የአፈር መሸርሸርና ድርቅ ለመከላከልም እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

በሁለተኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ለመትከል  የታቀደው 5 ቢሊዮን ችግኝ በሐምሌ ወር ውስጥ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ህዝቡ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ያደረገው ከፍተኛ  ርብርብ  አስቀድሞ ለመፈጸም ማስቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 6 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ አመልክተው ፤ በተጨማሪም ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ ተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ችግኝ ይዘጋጃል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ችግኝ ለመትከል ከፍተኛ ርብርብ እንዳደረጉ ሁሉ ሀገሪቱን  በሁሉም ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ ፋና ወጊ  ለማድረግ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ትብብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ከማይጠቅም ከፋፋይና የኔ ብቻ ከሚል አስተሳሰብ በመላቀቅ በብልጽግናው ጉዞ የሀገሪቱ ህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መላ ኢትዮጵያዊያን ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግስት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በቁርጠኝት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ እውን እንዲሆን ህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፍና እገዛ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚጠብቁት ታላቁ የህዳሴው ግድብ ዘላቂ ጥቅም እንዲረጋገጥ የአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።

በአማራ ክልል የሚተከል ችግኝ የህዳሴው ግድብ በደለል እንዳይሞላና ለዘላቂ ጥቅም እንዲውል በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።

በተለይም ዘንድሮ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት በድል የተጠናቀቀበት ወቅት በመሆኑ በከፍተኛ መነሳሳት የችግኝ ተከላ ስራው ተከናውኗል ብለዋል።

በአንድ ጀንበር ብቻ 190 ሚሊዮን ችግኝ እንደተተከለ ያመለከቱት  ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ  ዘንድሮ ለመትከል የታቀደው ከአንድ ቢሊዮን 600 ሚሊዮን  በላይ ችግኝ ማሳካት መቻሉን አሰታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የህዳሴው ግድብ ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብር መንገድ እንዲቀጥል በማድረግ ላበረከቱት አሰተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በባህር ዳር ዛሬ በተካሄደው ሀገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የማጠቃለያ ስነስርዓት የፌደራልና የክልል አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም