መንግሥት ከፅንፈኞች ጋር የሚሰሩ አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

73

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2012 (ኢዜአ) መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በውስጡ ተሰግስገው ከፅንፈኞች ጋር የሚሰሩ አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ አንድ ምሁር ጠየቁ።

መንግሥት ወቅትና ሁኔታ እየጠበቁ በሚከሰቱ ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውሶች ሕይወት ሲያልፍ፣ ንብረት ሲወድም፣ አገር ወደ አለመረጋጋት ስጋት ስትገባ የሕግ የበላይነትን ማስከበር  ሚናውን እንዳልተወጣ ይነገራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  አህመድ በቅርቡ ከፖለቲካ  ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው  ውይይት በመንግሥትና በተፎካካሪ ፖለቲካ ኃይሎች  ውስጥ  የተሰገሰጉ ጥቅመኞች  አገሪቱ  ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖራት ምክንያት ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም  የሕግ ማስከበር ሂደቱን በተመለከተ በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሕግና የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌን አነጋግሯል።

መንግሥት ከፅንፈኞች ጋር የሚሰሩ አመራሮችን ከውስጥ ባለማጥራቱ ዛሬም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ክፍተት ይታይበታል ብለዋል።

አንዳንድ አመራሮች ለዜጎች ሞትና ንብረት መውደም  ተጠያቂ  መሆን  እንደሚገባቸው  ምሁሩ አመልክተዋል።

በመሆኑም ራሱን በመፈተሽ ለጥቅም  አሳዳጅነት የተሰገሰጉ አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ዶክተር አልማው ጠይቀዋል።

መንግሥትም ሆነ ማንኛውም አካል በሐሳብ ልዕልና አሸንፎ አገርን ስለመምራት ቅድሚያ እንዲሰጡ የጠየቁት ምሁሩ፥ ዜጎችም የሚቀርቡላቸው አመለካከቶች መርምረው እንዲቀበሉም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም