የለውጡን ጉዞ ለማሳካት የድርሻችንን እንወጣለን... በድሬዳዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች

80

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 6/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በመሆን ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ።

ተወላጆቹ ይህንን የገለጹት በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና በሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ዙሪያ በድሬዳዋ ለሶስት ቀናት  በተዘጋጀው ስልጠና እየተሳተፉ ባሉበት ወቅት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ነው፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል  የቀድሞ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አመራር የነበረው ወጣት ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም እንደተናገረው በተለያዩ ውዥንብሮች ሣቢያ የትግራይ ተወላጆች ወደ ብልጽግና አለመቀላቀላቸው ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

አሁን ግን ቁርጠኛ በመሆን ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ህብረት በመፍጠር የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት ወስነናል ብሏል፡፡

ውሳኔው የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በብልጽግና ፓርቲ በመታቀፍ ተጠቃሚነታቸውን  ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግሮ፤ "ህውሃት አሁን የግለሰቦች መጠቀሚያ እንጂ የህዝብ አይደለም"ብሏል፡፡

ከብልጽግና ጋር በመሆን ለውጡን ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገረው ደግሞ   ወጣት ኤፍሬም ግርማይ ነው፡፡

በድሬዳዋ ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የሚሰጠው ስልጠና ለቀጣይ ጉዞ መደላደል የሚፈጥርና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ለሀገር ዕድገት፣ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ  ያግዛል ብለዋል፡፡

ወጣት ህይወት ገብረየስ በበኩሏ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተራማጅ ፣አካታች፣ የተሻለ ጸጋ የሚያመጣ ሃሳብ ያለው ህዝቡን መምራት እንደሚገባ ተናግራለች፡፡

ስልጠናው ከብልጽግና ጋር ለመቀላቀልና ለመስራት መደላደል እንደሚፈጥር ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ  ወጣት ፀጋዬ በርሄ ገልጸዋል።

በድሬዳዋ የተጀመረው ጉዞ በሌሎች የምስራቁ ክፍል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ወደ ብልጽግና እንዲቀላቀሉ መነቃቃት ይፈጥራል ብሏል፡፡

"ስለብልጽግና የሚነገረን  ወሬ የተሳሳተ መሆኑን ተረድቻለሁ፤ ይህንኑ የተረዳሁትን  ወደ ስልጠናው ለመምጣት ላልቻሉት በማስረዳት ከተሳሳተ አመለካከት ለመውጣት እሰራለሁ" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ለምለም ስዩም ናቸው፡፡

በስልጠናው ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ከድር ጁሃር ያለፈውን በይቅርታ በማለፍ በህብረት ወደ ብልጽግና መጓዝና ሀገሪቱን ከድህነት  ማላቀቅ የሁላችንም ኃላፊነት  ነው ብለዋል።

ለውጡን ለማደናቀፍ  የሚሰሩ የጥላቻ ፖለቲካ ነጋዴዎችን ወጣቶቹ እንዲታገሏቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

"ህብር ወደ ብልጽግና " በሚል መሪ ሃሳብ ፓርቲው ባዘጋጀው ስልጠና ከ300 በላይ የትግራይ ተወላጆች እየተሳተፉ ነው።

በቆይታቸውም በሀገሪቱ የለውጡ ጉዞና በብልጽግና ፓርቲ  ፕሮግራም ዙሪያ  ገለጻና ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም