የመንግስት ሰራተኛው ለከተማዋ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር መድረስ መትጋት አለበት -ታከለ ዑማ

53

አዳማ ነሐሴ 05/2012 (ኢዜአ) ፡- የመንግስት ሰራተኛው ህብረተሰቡን በመልካም ስነ-ምግባርና ተነሳሽነት በማገልገል በከተማዋ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ መትጋት እንዳለበት ተገለጸ፡፡

በአዳማ አባገዳ አደራሽ ላለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የከተማዋ አስተዳደር  መንግስት ሰራተኞች  የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ስነስርዓት የተገኙት ምክትል የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ዑማ በሰጡት የስራ መመሪያ ሰራተኛው በከፍተኛ ዲስፒልንና ሞራል ህብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅበታል ብለዋል።

በከተማዋ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር ማድረስ የሚችለው መልካም ስብእናን የተላበሰና ራሱን የሰጠ ሰራተኛ በየደረጃው ሲኖር መሆኑን ተናግረዋል።

የስልጠናው ዓላማም  የሰው ኃይሉን በአመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት በማብቃት የለውጡ ወሳኝ ተዋናይ እንዲሆን ማስቻል እንደሆነ አስታውቀዋል።

በዚህም ሀገራዊ ለውጡ የሚሳካው በተለይ ሰራተኛው ህብረተሰቡን በመልካም ስነ-ምግባርና ተነሳሽነት ማገልገል  ሲችል  መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው ስልጠናው የተዘጋጀውም ከአመለካከት ብዥታና የግንዛቤ እጥረት የሚመነጩ ክፍተቶችን ለማረም ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።

የመንግስት ሰራተኛው ህብረተሰቡን  በተገቢው በማገልገል ለከተማዋ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር መድረስ መትጋት እንዳለበት  ኢንጅነር ታከለ አሳስበዋል።

አስተዳደሩ የለውጡን አካሄድና አቅጣጫ በአግባቡ ተገንዝቦ ለፍሬያማነቱ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ የሚችል የሰው ኃይል ለመፍጠር እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ  የአስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና  የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ናቸው።

ለሰራተኛው ምቹ የስራ ቦታ ለመፍጠርና ለተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ  የነበረውን ልዩነት ማጥበብ መቻሉንም ጠቁመዋል።

በተለይ በአስተዳደሩ የነበረውን የኑሮ ውድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያ በሁለት ዙር ብቻ እንዲከፈል በማድረግ ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ብለዋል።

ከቀበሌ እስከ ክፍለ ከተማና አስተዳደሩ ድረስ ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማመቻቸት ከ60ሺህ በላይ  ሠራተኞች በስልጠና  እንደሚያልፉም ጠቁመዋል።

በአዳማ አባገዳ አዳራሽ   ሲካሄድ የቆየው ስልጠና  ኮሮናን ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን በስልጠናው ከ1ሺህ 200 በላይ ሰራተኞች መሳተፋቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም