የምንገነባው ስርዓት የምንመዘብርበት ሳይሆን አገልጋይነትን ለትውልድ የምናስተምርበት ነው

109

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2012  (ኢዜአ) የምንገነባው ስርዓት " ስልጣን ላይ እያለን የምንዘርፍበት ስንወርድ የምንሸሽበት ሳይሆን አገልጋይነትን ለትውልድ የምናስተምርበት ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሲቪክ ማህበራት አመራሮችና ተወካዮች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይ ከተሳታፊዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ብዙም ሳይቆዩ "አሳሪ ነው" ሲባል የሚተቸውን የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ህግ እንዲሻሻል ማድረጋቸውን በበጎ ጉኑ አንስተዋል።

ነገር ግን አዋጁ እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር አውርዶ ስራ ላይ በማዋል ረገድ አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ አንስተዋል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያሳየው "ሆደ ሰፊነት ትእግስት" ገደብ ሊኖረው እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

የሲቪክ ማህበራትና መንግስት የሰላምን ጉዳይ ለድርድር ሳያቀርቡ በቅንጅት መሰራት እንዳለባቸውም ነው ተሳታፊዎቹ ያነሱት።

ውይይት እየተደረገበት ባለው የመንግስት የ10 ዓመት መሪ አቅድ ላይ በሚገባው ልክ እየተሳተፈ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የጀመርነው ሪፎርም ተቋማት ሳይፈርሱ ባሉበት የመለወጥ ሂደት ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ አልፎ ችግሮች ማጋጠማቸው የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ የተሻለችና ሁሉንም ዜጎቿን በእኩል የምታቅፍ ሀገር እንገነባለን ብለዋል።

መንግስት ቀለል ብሎ በመቅረቡ አቅሙ የተዳከመ የሚመስላቸው አካላት እንደሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ነገር ግን የምንገነባው ስርዓት ስልጣን ላይ ስንወጣ የምንዘርፍበት፤ ስንወርድ የምንሸሽበት ሳይሆን አገልጋይነትን ለትውልድ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።

በቅረቡ በኦሮሚያ ክልል ለመናገር በሚያሳፍር መልኩ በርካታ ዜጎቻችን ሞተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት ይህን ተከትሎ የፖሊስ  አባላትን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አብራርተዋል።

በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ በዎሺች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጠር ስር ውለዋል ብለዋል።

ትናንት የተጸየፍነውን በደል ዛሬ ላይ የምንደግመው ከሆነ ከግጭት አዙሪት ልንወጣ አንችልም ሲሉም ነው የተናገሩት።

ግጭቱን የብሔር መልክ እንዳለው አድርጎ  የሚያራግቡ አካላት እንዳሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በግጭቱ በርካታ ኦሮሞዎች መሞታቸውን በአስረጂነት አንስተው፤ "ዋናው ነገር ግጭት ከተከሰተ መጀመሪያ የሚያጠቃው እኔን ነው የሚለውን  መገንዘብ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጥቂቶች የምትወከል ሳይሆን የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር መሆኗንም ነው የገለጹት።

ከዚህ አንጻር ጥቂት ሰዎች ሲያጠፉ ማህበረሰብን ጠቅልሎ መውቀስ አይገባም ሲሉም አብራርተዋል።

የሲቪክ ማህበራት ይህን በመገንዘብ በከተማ ሳይወሰኑ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ለሰላም መስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም