በአማራ ክልል ከበልግ እርሻ ከ2 ሚሊዮን 700ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተገኘ

292

ባህርዳር፣ ነሐሴ 5/ 2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከሁለት ሚሊዮን 700ሺህ ኩንታል በላይ የሰብል ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

በቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤልያስ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ የተገኘው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አራት ዞኖች ከለማው 182 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ነው።

“በምርት ወቅቱ 218 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ቢታቀድም በዝናብ መዘግየትና መቆራረጥ ምክንያት ማሳከት የተቻለው 83 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ ነው” ብለዋል።

በበልግ ወቅት ከለማው መሬት ከተገኘው የሰብል ዓይነት ምርት ውስጥ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ማሾ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄና ሽምብራ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የተገኘው የሰብል ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ካር ሲነጻጸር በ247 ሺህ ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በምርት ወቅቱ 8 ሺህ 195 ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በክልሉ በበልጉ ወቅት  በተካሄደው  የእርሻ ልማት   277 ሺህ አርሶ አደሮች  ተሳትፈዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ41 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ሰይድ በሰጡት አስተያየት በበልጉ ወቅት ካለሙት ማሳ በዝናብ መቆራረጥ ምክንያት የጠበቁትን ያህል ባይሆንም  ስምንት ኩንታል የስንዴ፣ ጤፍና ገብስ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋልል።

በዘንድሮው የበልግ ዝናብ ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ገብስና ስንዴ ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳው አርሶ አደር አደም አሊ ናቸው፡፡

ተሰብስቦ ከተወቃው  የስንዴ ሰብል ብቻ አራት ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን  አርሶ አደሩ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል  በ2011 የበልግ ወቅት ከለማው መሬት ከሁለት ሚሊዮን 400ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።