በዓሉ ለወጡን በሚያጠናክሩ ተግባራት እንዲከበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አመራሮች ገለጹ

71

ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 5/2012 (ኢዜአ) 15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ለወጡንና የህዝቦችን የእርስ በርስ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ተግባራት እንዲከበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የክልሎችና የፈደራል ተቋማት አመራሮች ገለጹ።

በመጪው ህዳር በድሬዳዋ ለሚከበረው በዓል በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ የበዓሉ አስተባባሪ አብይ ኮሚቴ ትናንት ተወያይቶ የፌደራልና የአዘጋጇን የድሬዳዋ ዕቅዶች አጽድቋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ እንደተናገሩት፤ በዓሉ የሀገሪቱን ህዝቦች በእኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነታቸውን በሚያጎለብቱ ተግባራት ይከበራል፡፡

በፌደራል ስርዓቱ ሰፊ የአስተምህሮት ተግባራትና በህገ-መንግስቱ ላይ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥሩ ሥራዎች  እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

በተለይ የበዓሉ ሲምፖዚየሞች ላይ የሚቀርቡት ፅሁፎች ሰፊ ጊዜ ተወስዶ የሚዘጋጁ በመሆናቸው የህዝብን የእርስ በርስ ትስስርና የአብሮነት እሴቶች ለማስቀጠል እንደሚያግዙ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዋና አጀንዳዎች ይሆናል ብለዋል፡፡

በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ለውጥ ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ስኬት  ከአዘጋጁ ከተማ ድሬዳዋ ጋር በመተባበር በሁሉም ዘርፍ አስፈላጊው ዕገዛ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ አሁን ባለበት ከቀጠለ ቴክኖሎጂና ሚዲያዎችን በስፋት በመጠቀም በዓሉ በጥንቃቄ የሚከበርበት መንገድ ለማመቻቸት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

የኮሚቴው አባል አቶ በዛብህ ገብረየስ በዓሉ ኢትዮጵያዊያንን  በማገናኘት የሀገራቸውን አንድነት ጠብቀው እንዲተሳሰሩ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለበዓሉ የሚሆኑ ፅሁፎች በምሁራን እንዲዘጋጁ በማድረግ በወጣቱ ሥነ-ምግባርና እሴት ግንባታዎች ላይ የሚያጠነጥኑ ቢሆኑ ይመረጣል ብለዋል፡፡

ለበዓሉ መሳካት ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው፤ በዓሉ አስተማማኝ ሰላምና የህግ የበላይነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ማክበር ይገባል ብለዋል፡፡

በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ተለይተው የሚወጡበት ሰፊ ውይይቶች ማድረግ ፣ የደም ልገሳ ፣ የህዳሴ ግድብ ፣ የአረንጓዴ አሻራ እንደ ዋና አጀንዳዎች የበዓሉ ማጠንጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሀገር በድሬዳዋም ሆነ በየክልሉ ለሚከበረው በዓል ማማርና መሳካት የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው በዓሉ ሲከበር የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ በሚያጠናክሩና የኢትዮጵያ ብልጽግና ይዘው በሚቀጥሉ ወጣቶች ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለዚህ ታላቅ በዓል ስኬት አስፈላጊው ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፈጡም ሙስጠፋ በዓሉ ድሬዳዋ ከምስራቅ ተጎራባችም ሆነ ከመላው የሀገሪቱ ክልሎች ጋር ያሏትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያግዛታል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ ዘመን የተሻገሩትን የፍቅር፣ የአብሮነትና የመከባበር እሴቶች ለማጠናከርም በዓሉ ልዩ አጋጣሚ የሚፈጥርና ሀገራዊ ለውጡን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ለወጡንና የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ተግባራት እንዲከበር በመደገፍ ኃላፊነታቸው እንደሚወጡ  አመራሮች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የሁሉም ክልሎች፣ የድሬዳዋና አዲስ አበባ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች እንዲሁም የፌደራል ተቋማት አመራሮች  በዓሉ "የህዝቦች እኩልነትና አንድነት ለጋራ ብልጽግና " በሚል መሪ ሃሳብ እንዲከበር በአብልጫ ድምጽ ወስነዋል፡፡

14ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ  መከበሩ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም