የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለጎንደር ዩንቨርሲቲ ሆሰፒታል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

163

ጎንደር ነሐሴ 4/2012 (ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ግምታቸው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ለኮሮና መከላከል ስራ የሚውሉ መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ለጎንደር ዩንቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆሰፒታል ዛሬ ድጋፍ አደረገ ፡፡ 

በድጋፍ ርክክቡ ስነስርዓት ወቅት ማህበሩ የጎንደር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አቶ አታለል ታረቀኝ እንደተናገሩት ለሆስፒታሉ ከተለገሱት ቁሳቁሶች መካከል 20 የህሙማን አልጋዎችና ፍራሾች  ፣ ከ5ሺ በላይ የፊትና የአፍንጫ ጭንብሎችና  ጓንቶች ይገኙበታል፡፡


የህሙማን ማመላለሻ "ስትሬቸሮች" እና የህመም ማስታገሻዎች  እንዳሉበት ጠቁመው ማህበሩ ድጋፉን ያደረገው ከአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ያገኘው መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ቁሳቁሶቹን የተረከቡት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው "ድጋፉ ሆስፒታሉ ለሚያከናውነው የኮሮና ምርመራና የህክምና አገልግሎት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡


ማህበሩ ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር ሆስፒታሉ ላቋቋመው የኮሮና ህክምና መስጫና ማቆያ ማዕከልየቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

በህክምና ማዕከሉ በየቀኑ ከ50 በላይ የጤና ባለሙያዎች ለኮሮና ህሙማን ተገቢውን የህክምና ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን  አመለክተዋል።


ሆስፒታሉ ያቋቋመው የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያም በቀን ከ400 በላይ ናሙናዎችን በመቀበል እየሰራ  እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡


የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከዚህ ቀደም በማዕከላዊ ፣ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለተቋቋሙ የኮሮና ህሙማን ማቆያና ህክምና መስጫ ማዕከላት ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማበርከቱም ተገልጾአል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም