በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ዲያስፖራዎች ጠየቁ

75

ሀዋሳ ነሐሴ 04/2012 (ኢዜአ) በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ያሉባቸውን ውጣ ውረድ የበዛበት አሰራር በማስተካካል ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው በደቡብ ክልል የሚገኙ ዲያስፖራዎች ጠየቁ።

የክልሉ የዲያስፖራ ፣ አጎራባች ክልሎች ፣ ፕሮቶኮል ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዲያስፖራው የልማት ተሳትፎ ዙሪያ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።

በውይይት መድረኩ የደቡብ ክልል ዲያስፖራ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አለምሰገድ ይፍሩ እንዳሉት በውጭ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ከለውጡ በኋላ ወደ ሀገራቸው እየገቡ ቢሆንም በሀገሪቱ ዕድገት ላይ እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ውስን ነው።

ይህንን ለማስተካከል ከሌሎች ሀገራት ልምድ መቅሰምና ያሉ ችግሮችን ፈትሾ መፍታት እንደሚገባ አመልክተው የሀገሪቱ ዲያስፖራ የዘመቻ መሰል ጊዜያዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይ ዲያስፖራውን በሚመለከት የሚከናወኑ ሥራዎች እና ዕቅዶች ወጥነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በየአካባቢው የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች እንዲሁም ዲያስፖራው በሀገር ውስጥ ለመቆየት የሚችልበትን አጭር ጊዜ ያላገናዘቡ ውጣ ውረድ የበዛበት አሰራር  መንግስት በማስተካካል ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል።

በፌዴራልና ክልሎች ላይ ብቻ ተንጠልጥለው ያሉ አሰራሮችም እስከ ታችኛው መዋቅር ተዘርግተው የተቀላጠፈ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መደላደል ሊኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ዲያስፖራ አቶ ተሾመ ተክሌ በበኩላቸው በ2007 ዓ.ም የኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ አቅርበው እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የአስፈፃሚ አካላት የግልፀኝነት ችግር በተለይ በታችኛው መዋቅር በስፋት እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

በይይት መድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር አባተ የሥጋት ያካሄዱት ጥናት በክልሉ የሚገኙ ዲስፖራዎች በልማት የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ እንዳያበረክቱ በአስፈፃሚው አካልና በራሳቸው በኩል ያሉ ማነቆዎች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

በመንግስት በኩል ሊፈቱ የሚገባቸው የድጋፍና ክትትል እንዲሁም ሰፊ የመሰረተ ልማትና ውጣ ውረድ የበዛበት አሰራር ችግሮች እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል።

ለአሰራር ምቹ ያልሆኑ የሕግ ማዕቀፎች እንዳሉ ጠቁመው የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ በቀጣይ ችግሮቹ ሊጤኑና ሊፈቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በዲስፖራዎች በኩል ለኢንቨስትመንት የተረከቡትን መሬት አጥሮ ለረጅም ጊዜያት ያለስራ ማቆየትን ጨምሮ መስተካከል ያሉባቸው ክፍተቶች ናቸው ብለዋል።

የፓናል ውይይቱን የመሩት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ጥናቱ መሬት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሚገባ የለየ መሆኑን ገልፀዋል።

ዲያስፖራው በልማቱ ማበርከት ያለበትን አስተዋፅኦ በሚገባ እንዳያበረክት ማነቆ የሆኑበትን ችግሮች ለመፍታት አቅዶ መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ርስቱ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሀብቶችን ለማበረታታት በመንግስት በኩል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአሰራር አመቺ ያልሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እንዲቻል ሕጎችን የመፈተሽ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በ2013 በጀት ዓመት በክልሉ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል የዲያስፖራዎች ጉዳይ አንዱ እንደሆነም አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ በቅድሚያ በክልሉ የሚገኙ ዲያስፖራዎችን የመለየትና ቀርቦ በጋራ የመስራት፣ ችግሮቻቸውን ፈትሾ በመፍታት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ዴስኩን በዕውቀት እንዲመራ በማድረግ አሰራሩ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ወጥ አድረጎ መምራት ሌላው የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል።