በቤንች ሸኮ ዞን ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማሰባሰብ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ተጀመረ

60

ሚዛን፣ ነሐሴ 4/2012 (ኢዜአ) በቤንች ሸኮ ዞን ማህበረሰቡን በማስተባበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማሰበሰብ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ተጀመረ።
ባለፈው ዓርብ በተጀመረው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት  አራት ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የዞኑ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ኡክሪያብ እንደገለጹት የዞኑ ህዝብ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቦንድ ግዥ፣ በገንዘብና  ዓይነት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በዚህም  በዓይነትና በገንዘብ ከህብረተሰብ ከተለያዩ ተቋማት ከ38  ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አውስተዋል።

ቃል ተገብቶ ያልተሰበሰበን ቀሪ ገንዘብ  የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ዙር የግድቡን ውሀ ሙሌት መነሻ በማድረግ የተፈጠረውን መነቃቃት በመጠቀም ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ታምሩ  ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ  "ግድቡ የእኔ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት እንደተጀመረና አራት ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ  አቶ ታጠቅ አሰፋ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ለመውጣት ተስፋ አድርገን በተባበረ አቅም እየገነባ ነው እንገኛለን ብለዋል፡፡

ግድቡን በራስ አቅም እየተሰራ እንዳለው ሁሉ ማንም በግንባታው ሂደትም ሆነ በውሀ ሙሌቱ ጣልቃ ሊገባብን አንፈቅድም ሲሉም ገልጸዋል።

ለአራት ዓመታት ያለ ወለድ ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቀጣይም እንደሚደግፉ አቶ ታጠቅ ተናግረዋል፡፡

በመላ ኢትዮጵያውያን እየተገነባ የሚገኘው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ ሌላው  የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙራድ አህመድ ናቸው።

መንግስት በግድቡ ግንባታ ላይ የውጭ  ጣልቃ ገብነትን ወደ ጎን በማለት የያዘው አቋም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ግድቡ የገጠሙትን የአሠራር ችግሮች በመፍታት በስኬት ማስቀጠል መቻሉም መንግስት ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ያለውን ጠንካራ አቋም ያሳየበት እንደሆነም አመልክተዋል።

በተጀመረው የውሀ ሙሌቱ የተገኘውን ድል ለማጠናከር በቦንድ ግዥ  ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም