በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አሜሪካዊ ዜግነታቸውን እየመለሱ መሆናቸውን ጥናት አመለከተ

67

 አዲስ አበባ  ነሀሴ 4/2012 (ኢዜአ) በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አሜሪካዊ ዜግነታቸውን እየመለሱ መሆናቸውን አዲስ ጥናት አመለከተ።  

ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው እ.አ.አ በ2020 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ5 ሺህ 800 በላይ አሜሪካውያን ዜግነታቸውን መመለሳቸው ጥናት አመላክቷል።

ይህም እ.አ.አ በ2019 ዜግነታቸውን ከመለሱ 2 ሺህ 72 ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ መጨመሩ ተገልጿል።

ጥናቱን ያካሄደው ‘ባምብሪጅ አካውንታንትስ’  ለሲ ኤን ኤን እንደገለጸው ዜግነታቸውን የመለሱት ሰዎች በአብዛኛው አሜሪካን የለቀቁና ‘በአሜሪካ ያለው ሁሉ ነገር በቃኝ’ ያሉ ናቸው።

በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አመራር ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃዎች እንዲሁም በአገሪቱ ፖሊሲዎች  ቅር መሰኘታቸው ዜግነታቸውን ለመቀየራቸው በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

የአሜሪካ የታክስ ፖሊሲም ሌላው አሜሪካውያን ዜግነታቸውን እንዲመለሱ ያደረጋቸው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ከአሜሪካ ውጭ ቢኖሩም በየአመቱ የውጭ አገር የባንክ ሂሳባቸውን፣ የኢንቨስትመንት፣ ጡረታቸውንና ሌሎች ተያያዥ ሂሳቦቻቸውን ለአሜሪካ መንግስት የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው በዘገባው ተጠቅሷል።

እነዚህ ሰዎች በዜግነታቸው የሚያገኟቸው ክፍያዎች ቢኖርም በአመታዊው የታክስ ሪፖርት ግን መማረራቸው ነው የተጠቀሰው።

በዘገባው እንደተመለከተው ዜግነታቸውን መመለስ የፈለጉ ሰዎች 2 ሺህ 350 ዶላር መክፈልና በሚኖሩበት አገር ወደ ሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ በአካል መቅረብ ይኖርባቸዋል።

አሜሪካዊ ዜግነትን መመለስ ውጣ ውረዶች ቢኖሩትም ዜግነትን የመመለስ ልምዱ እየጨመረ እንደሚሄድ ጥናቱን ያካሄደው ተቋም ትንበያ ያመለክታል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በመጪው ህዳር ወር በአሜሪካ የሚካሄደውን ምርጫ እየተጠባበቁ መሆኑንና ፕሬዝዳንት ትራምፕ በድጋሚ የሚመረጡ ከሆነ ዜግነታቸውን የሚመለሱ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ የሚል እምነት መኖሩንም ተቋሙ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም