አገራቱ የፈጠሩት ሰላም የአፋርን ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ስለሚያረጋግጥ እንደሚደግፉት ነዋሪዎች ገለጹ

61
ሰመራ ሓምሌ 4/2010 በኢትዮ-ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም የአፋርን ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ እንደሚደግፉት የሰመራ ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር ቀደምነት በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ቅራኔ ተፈቶ አዲስ ግንኙነት እንዲጀምሩ መደረጉ በተለይ ድንበር አካባቢ ላሉ የሁለቱ አገራት ዜጎች ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። የሎግያ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኡመር ኢብራሂም እንዳለው የአፋር ክልል ህዝብ ከኤርትራ ጋር በድንበር ብቻ ሳይሆን በባህል፣ በሃይማኖትና በደም የተገናኘና የተሳሳረ ወንድማማች ህዝብ ነው። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው አለመግባባት በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አመራር በአጭር ግዜ ተፈቶ አገራቱ ወደ ቀድሞ ወዳጅነታቸው እንዲመለሱ መደረጉ ድንገተኛ ክስተት እንደሆነበት ተናግሯል። አገራቱ ወደ ሰላም መመለሳቸው የአፋር ህዝብ የጀመረውን የሰላምና የልማት ጉዞ ከማፋጠን ባለፈ በቀጣይ የአገራቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ስለሚያደርግ እንደሚደግፈው ገልጿል። " አገራቱ ሰላም መፍጠራቸው ተወልጄ ካደኩበት አካባቢ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉ ኤርትራውያን የልጅነት ጓደኞቼ ጋር ዳግም በአካል ለመገናኘት ተስፋ እንድሰንቅ አድርጎኛል" ብሏል። የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኢጋህሌ አሊ በበኩሉ "ለዘመናት ሲንከባለል የቆየውን የሁለቱ አገራት የድንበር ችግር ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የመሪነት ሚና ወስደው ያስመዘገቡት ውጤት ኢትዮጵያ ሰላም ወዳድ መሆኗን ዳግም ለዓለም ህዝብ ያረጋገጠ ነው" ብሏል። እንደ ቡሬ፣ ማንዳ እና መሰል ያሉ የአፋር ክልል ከተሞች በስጋት ቀጠና ውስጥ በመቆየታቸው እየተዳከሙ መምጣታቸውን አስታውሰው፣ አገራቱ ወደ ሰላም መምጣታቸው የከተሞቹ እድገትና የነዋሪዎችም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዳግም እንዲያንሰራራ ተስፋ መፈንጠቁን ተናግረዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዳግም እርቅ መውረዱ እንዳስደሰተው የገለጸው ወጣቱ  አሰብ ከሚገኙ እህትና ወንድሞቹ ጋር  በስልክ መገናኘት መጀመሩን ተናግሯል።። " በቅርቡም አሰብ ድረስ በመሄድ ቤተሰቤን ለማየት በመጓጓቴ ዝግጅት እያደረኩ ነው፤ ቤተሰቦቼን ሳገኝ ዳግም እንደተወለድኩ እቆጥረዋለሁ" ብሏል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት ሴቶች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ በማህበራዊ አገልግሎቶችም ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዛህራ መሀመድ ናቸው። ወይዘሮ ዛህራ እንዳሉት አገራቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላም መምጣታቸው ለዘመናት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች ዳግም እንዲገናኙ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ለማጠናከር ያስችላል። ከእዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ህዝቦች እብሮ ለማደግና ድህነትን ለማሸነፍ ለጀመሩት ጥረት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸውና በድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎች ሰላምን ያለስጋት እንዲያጣጥሙ የሚያደርጋቸው መሆኑ ገልጸዋል። " በዶክተር አብይ አህመድ ለተመራው የልዑካን ቡድን ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ የተደረገው ቤተሰባዊ ደማቅ አቀባበል ሁለቱ ህዝቦች ምን ያክል የተሳሰሩና ፍቅር እንዳላቸው መረዳት ይቻላል " ያለው ደግሞ የሎግያ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብዱ አሊ ነው። ያለማንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ሁለቱ አገራት እርቅና ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠራቸው በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ችግሮችን በውይይትና በፍቅር መፋታት እንደሚቻል አስተማሪ መሆኑን ገልጿል። ከእዚህ በተጨማሪ የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከርና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም