በድሬዳዋ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል

78

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 4/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር አስተማማኝ ሰላም የማስፈንና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ አስታወቁ።

በከተማው ገንደቆሬ ቀበሌ በፖሊስና በነዋሪዎች ትብብር የተቋቋሙ ሁለት የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ተቋማት  ትናንት ተመርቀው አገልግሎት ጀምረዋል ።

የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽነር በወቅቱ እንደገለጹት  የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በከተማው ሁከት በመፍጠርና ንብረት በማውደም እጃቸው ያለበት አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እየቀረቡ ነው።

ፖሊስ ከጥፋቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሎ ለህግ እየቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

"ፖሊስ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ሥራ በማጠናከር ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን በቁርጠኝነት ይሰራል" ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት የከተማውን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ማድረግ  እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የገንደ ቦዬ ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ዚያድ መሐመድ ወጣቱ ከፖሊስ ጋር በመሆን ባለሀብቶችንና ሌሎች ነዋሪዎችን  በማስተባበር የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ተቋማት ማቋቋማቸውን ተናግሯል።

"ተቋማቱ ነዋሪውና ፖሊስ በመቀናጀት በከተማው የተሻለ ሰላም ለማስፈን እያደረጉ ያለውን ጥረት ያግዛሉ" ብሏል።

የተደራጁ 30 ወጣቶች በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር  ቦታ ላይ እያከናወኑ ያሉት የብሎኬት ምርትና ሌሎች ስራዎች በተቋማቱ የምረቃ ስነ- ስርዓት   ወቅት ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም